ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ አስከትሎ ወደ ከፍተኛ ተራራ ላይ ወጣ፤ በፊታቸውም መልኩ ተለወጠ። ልብሱ እጅግ አንጸባረቀ፤ በዓለም ላይ ማንም አጣቢ ያን ያኽል ሊያነጣ እስከማይችል ድረስ ነጭ ሆነ። በዚያን ጊዜ ኤልያስና ሙሴ ተገልጠው ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ! እዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። ሦስቱ ደቀ መዛሙርት እጅግ ደንግጠው ስለ ነበር ጴጥሮስ የሚናገረውን አያውቅም ነበር። ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፦ “የምወደው ልጄ ይህ ነው! እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ ተሰማ ወዲያውም ዞር ብለው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ከተራራውም ሲወርዱ ኢየሱስ፦ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ይህን ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ሲል አዘዛቸው። ቃሉንም ሰምተው በልባቸው ያዙት፤ ይሁን እንጂ “ይህ ከሞት መነሣት ምን ማለት ይሆን?” እያሉ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። እነርሱም፦ “የሕግ መምህራን መጀመሪያ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ስለምን ይላሉ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “እርግጥ ነው፤ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ያስተካክላል፤ ይሁን እንጂ፥ የሰው ልጅ ከባድ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚናቅ የተጻፈው እንዴት ነው? እኔ ግን ኤልያስ ቀደም ብሎ መጥቶአል፤ ሰዎችም ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው የፈለጉትን ሁሉ አድርገውበታል” እላችኋለሁ። ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ወደቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው በመጡ ጊዜ ብዙ ሰዎች በዙሪያቸው ተሰብስበው አዩ፤ የሕግ መምህራንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይከራከሩ ነበር። ሕዝቡም ሁሉ ኢየሱስን ባዩት ጊዜ በመገረም ተደናገጡ፤ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት። ኢየሱስም “ከእነርሱ ጋር የምትከራከሩት በምን ጉዳይ ነበር?” ሲል ጠየቃቸው። ከሕዝቡም መካከል አንዱ፥ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መምህር ሆይ፥ ድዳ በሚያደርግ መንፈስ የተያዘውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በሚነሣበትም ጊዜ ይጥለዋል፤ አፉም ዐረፋ እየደፈቀ ጥርሶቹን ያፋጫል፤ ሰውነቱም ደርቆ እንደ በድን ይሆናል፤ ርኩሱንም መንፈስ እንዲያስወጡለት ደቀ መዛሙርትህን ጠይቄአቸው ነበር፤ ነገር ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታምኑ ሰዎች! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” እነርሱም ልጁን ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩሱም መንፈስ ኢየሱስን ባየ ጊዜ ወዲያው ልጁን ጥሎ አንፈራገጠው፤ ልጁም በመሬት ላይ እየተንከባለለ ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፥ “ይህ በሽታ ከጀመረው ምን ያኽል ጊዜ ነው?” ሲል ጠየቀው። አባትየውም እንዲህ አለ፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው። ሊገድለውም እየፈለገ ብዙ ጊዜ በእሳትና በውሃ ውስጥ ይጥለዋል፤ ግን አንዳች ነገር ማድረግ ብትችል እባክህ እዘንልን! እርዳንም!” ኢየሱስም “ብትችል” ትላለህን? “ለሚያምን ሰው ሁሉ ነገር ይቻላል!” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፥ “ማመንስ አምናለሁ፤ ግን ማመን በሚያቅተኝ ነገር ሁሉ ደግሞ አንተ እርዳኝ!” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ እየተራወጡ ሲመጡ አየ፤ ርኩሱንም መንፈስ “አንተ ድዳና ደንቆሮ መንፈስ ከልጁ እንድትወጣ ወደ እርሱም ተመልሰህ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ልጁንም በጣም ካንፈራገጠው በኋላ ወጣ፤ ልጁም ልክ እንደ በድን በመሆኑ ብዙዎቹ የሞተ መሰላቸው። ኢየሱስ ግን የልጁን እጅ ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ። ኢየሱስም ወደ ቤት በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ፦ “ለመሆኑ ይህን ርኩስ መንፈስ እኛ ልናስወጣው ስለምን አልቻልንም?” ብለው ለብቻው ጠየቁት። እርሱም “እንዲህ ዐይነቱ በጸሎትና [በጾም] ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም አይወጣም።” ሲል መለሰላቸው።
የማርቆስ ወንጌል 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 9:2-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos