ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ መጡና ከእርሱ ጋር መከራከር ጀመሩ፤ ሊፈትኑትም አስበው ከሰማይ አንድ ተአምር እንዲያሳያቸው ጠየቁት። ኢየሱስ በመንፈሱ በመቃተት፦ “የዚህ ዘመን ትውልድ ተአምር እንዲደረግለት ስለምን ይፈልጋል? በእውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ተአምር አይደረግለትም!” አላቸው። ትቶአቸውም እንደገና በጀልባ ሆኖ ወደ ማዶ ተሻገረ። ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ በጀልባው ውስጥ ከአንድ እንጀራ በቀር ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም “ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠንቀቁ፤” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም “ይህን ማለቱ፥ ምናልባት እንጀራ ስለሌለን ይሆናል፤” ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ኢየሱስም ይህንኑ ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እንጀራ ስለሌለን ነው ብላችሁ ስለምን ታስባላችሁ? ገና ምንም የማታስተውሉና የማይገባችሁ ናችሁን? ልባችሁስ ገና እንደ ደነዘዘ ነውን? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮስ እያላችሁ አትሰሙምን? እንዴትስ ትዝ አይላችሁም? ለመሆኑ አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” እነርሱም “ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ” አሉት። “እንዲሁም ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ ሰዎች በቈረስሁ ጊዜ ትራፊውን ስንት መሶብ ሙሉ አነሣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሰባት መሶብ ሙሉ” አሉት። እርሱም “ታዲያ፥ ገና አታስተውሉምን?” አላቸው። ወደ ቤተ ሳይዳም በደረሱ ጊዜ ሰዎች አንዱን ዕውር ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እንዲዳስሰውም ለመኑት። እርሱም ማየት የተሳነውን ሰው እጅ ይዞ እየመራ ከመንደር ወደ ውጪ አወጣው፤ በሰውየውም ዐይኖች ላይ ምራቁን እንትፍ ብሎ እጁን ጫነበትና “አንዳች ነገር ታያለህን?” ሲል ጠየቀው። ዐይነ ስውሩም ቀና ብሎ፥ “አዎ ሰዎች ይታዩኛል፤ ግን እንደሚራመዱ ዛፎች ይመስላሉ፤” አለ። እንደገናም ኢየሱስ በሰውየው ዐይኖች ላይ እጁን ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ሰውየው ትኲር ብሎ አየ፤ ድኖም ሁሉን ነገር አጥርቶ ማየት ጀመረ። ከዚያም በኋላ ኢየሱስ “ወደ መንደሩ አትግባ፤” ብሎ ወደ ቤቱ እንዲሄድ አሰናበተው።
የማርቆስ ወንጌል 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 8:11-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች