የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 8:11-26

ማርቆስ 8:11-26 NASV

ፈሪሳውያንም ወጥተው ከኢየሱስ ጋራ ይከራከሩ ጀመር። ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳይ ጠየቁት። እርሱም በመንፈሱ እጅግ በመቃተት፣ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም!” አለ። ከዚያም ትቷቸው በጀልባ ወደ ማዶ ተሻገረ። ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ፣ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት የምትነጋገሩት ስለ ምንድን ነው? አሁንም አታስተውሉምን? ልብ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? ዐምስቱን እንጀራ ለዐምስት ሺሕ ሰው በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፣ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺሕ በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት። እርሱም፣ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን?” አላቸው። ከዚያም ወደ ቤተ ሳይዳ መጡ፤ ጥቂት ሰዎችም አንድ ዐይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ለመኑት። እርሱም የዐይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከሰፈር ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎበት፣ እጁንም በላዩ ጭኖ፣ “ምን የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፣ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ። ኢየሱስም እንደ ገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ። ከዚያም፣ “ወደ መንደሩ አትግባ! በመንደሩም ለማንም አትናገር” ብሎ ወደ ቤቱ ሰደደው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች