ሕዝቡንም እንደገና ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ሁላችሁም በማስተዋል አዳምጡኝ፤ ሰውን የሚያረክሰው፥ ከሰው የሚወጣው ነገር ነው እንጂ ከውጪ ወደ ሰው የሚገባውስ አያረክሰውም! [እንግዲህ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”] ኢየሱስ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተም ደግሞ ይህን አታስተውሉምን? ከውጪ ወደ ሰው የሚገባ ነገር ሰውን ምንም እንደማያረክሰው አይገባችሁምን? በሆድ በኩል ተላልፎ ወደ ውጪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይሄድም፤”። በዚህም ኢየሱስ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጸ። ቀጥሎም እንዲህ አለ፦ “ሰውን የሚያረክሱት ከሰው ልብ የሚወጡት ነገሮች ናቸው። እነርሱም፦ ክፉ ሐሳብ፥ ዝሙት፥ ስርቆት፥ ሰውን መግደል፥ አመንዝራነት፥ ስግብግብነት፥ ክፋት፥ አታላይነት፥ ስድነት፥ ምቀኝነት፥ ሐሜተኛነት፥ ትዕቢት፥ ግዴለሽነት ናቸው። ይህ ሁሉ ክፉ ነገር ከሰው ልብ ይወጣል፤ ሰውንም ያረክሰዋል።” ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ በጢሮስ ከተማ አጠገብ ወዳለው መንደር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤትም ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም ሰው እንዳያውቅ ፈለገ፤ ይሁን እንጂ ሊሰወር አልተቻለውም። ልጅዋ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ ኢየሱስ ሰምታ ወዲያውኑ መጣችና በእግሩ ሥር ወደቀች። ሴትዮዋም ከሲሮፊኒቃውያን ወገን የሆነች ግሪካዊት ነበረች፤ እርስዋ ከልጅዋ ጋኔን እንዲያወጣላት ኢየሱስን ለመነችው። ኢየሱስ ግን፥ “የልጆችን ምግብ ወስዶ ለውሾች መስጠት አይገባምና እስቲ ልጆቹ አስቀድመው ይጥገቡ፤” አላት። እርስዋም “እርግጥ ነው ጌታዬ፤ ግን ውሾችም እኮ በገበታ ሥር ሆነው ልጆች ሲበሉ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤” ስትል መለሰችለት። ስለዚህ ኢየሱስ፥ “በዚህ አነጋገርሽ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል፤ እንግዲህ ወደ ቤትሽ ሂጂ!” አላት። እርስዋም ወደ ቤትዋ በተመለሰች ጊዜ ልጅዋን ጋኔኑ ለቋት በአልጋ ላይ በደኅና ተኝታ አገኘቻት። ኢየሱስ የጢሮስን አካባቢ ትቶ ሄደ፤ በሲዶና በኩልም አድርጎ ዐሥር ከተሞች በሚባለው አገር ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። በዚያ አንድ ደንቆሮና ድዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት። ኢየሱስም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ወሰደና ጣቶቹን በሰውየው ጆሮዎች ውስጥ አገባ፤ ምራቁንም እንትፍ ብሎ የሰውዬውን ምላስ ዳሰሰ፤ ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና ሰውየውን “ኤፍታህ!” አለው፤ ፍቺውም “ተከፈት!” ማለት ነው። ወዲያውኑ ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ አንደበቱም ተፈታ፤ ያለአንዳች ችግርም አጥርቶ መናገር ጀመረ። ኢየሱስ ይህን ነገር ለማንም እንዳይናገሩ ሰዎቹን አዘዛቸው፤ ይሁን እንጂ፥ እንዳይናገሩ ባዘዛቸው መጠን በብዙ አብልጠው ያወሩ ነበር። የሰሙትም ሁሉ እጅግ በጣም በመደነቅ፦ “ሁሉን ነገር በመልካም አደረገ! ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፥ ድዳዎች እንዲናገሩ ያደርጋል!” አሉ።
የማርቆስ ወንጌል 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 7:14-37
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች