ደግሞም ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙኝ፤ ሁላችሁም አስተውሉ፤ ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን ሰውን የሚያረክሰው ከራሱ ወደ ውጭ የሚወጣው ነገር ነው፤ [ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።”] ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እርሱም፣ “እናንተም አይገባችሁምን? ከውጭ ወደ ሰው ገብቶ ሊያረክሰው የሚችል አንዳች ነገር የለም፤ ወደ ልቡ ሳይሆን ወደ ሆዱ ይገባል፤ ከዚያም ከሰውነቱ ይወጣልና።” ኢየሱስ ይህን በማለቱ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጠ። ቀጥሎም፣ እንዲህ አለ፤ “ከሰው የሚወጣ ያ ሰውን ያረክሰዋል፤ ከውስጥ፣ ከሰው ልብ የሚወጡት ክፉ ሐሳብ፣ ምንዝር፣ ስርቆት፤ ሰው መግደል፣ ዝሙት፣ መስገብገብ፣ ክፋት፣ ማታለል፣ መዳራት፣ ምቀኛነት፣ ስም ማጥፋት፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸው። እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከውስጥ ይወጣሉ፤ ሰውንም ያረክሱታል።” ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስ አገር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤት ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም እንዳያውቅበት ፈለገ፤ ሆኖም እዚያ መኖሩ ሊሸሸግ አልቻለም። ወዲያው ግን ትንሺቱ ልጇ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ወደቀች። ሴትዮዋም ግሪካዊት፣ በትውልዷም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች። እርሷም ኢየሱስ ጋኔኑን ከልጇ እንዲያስወጣላት ለመነችው። እርሱ ግን፣ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል ተገቢ ስላልሆነ፣ መጀመሪያ ልጆቹ ጠግበው ይብሉ” አላት። እርሷም መልሳ፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ ውሾችም እኮ ከገበታ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለችው። እርሱም፣ “ስለዚህ ይህን ስላልሽ ሂጂ፤ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷል” አላት። እርሷም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ ዐልጋ ላይ ተኝታ፣ ጋኔኑም ለቅቋት አገኘቻት። ከዚያም ኢየሱስ ከጢሮስ አገር ተነሥቶ፣ በሲዶና በኩል አድርጎ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር በማለፍ ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። በዚያም ሰዎች ደንቈሮና ዲዳ የሆነ አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት። ኢየሱስም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ከወሰደው በኋላ፣ ጣቶቹን በጆሮው አስገባ፤ ከዚያም እንትፍ ብሎ የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ። ወደ ሰማይም ተመልክቶ ቃተተና፣ “ኤፍታህ!” አለው፤ ይኸውም፣ “ተከፈት” ማለት ነው። ወዲያውም ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ ምላሱም ተፈትቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ። ኢየሱስ ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ሆኖም እርሱ እንዳይናገሩ ባዘዛቸው መጠን፣ ነገሩን አስፍተው አወሩት። ሕዝቡም ከመጠን በላይ በመደነቅ፣ “ያደረገው ሁሉ ጥሩ ነው፤ ደንቈሮዎች እንዲሰሙ፣ ድዳዎች እንዲናገሩ እንኳ አድርጓል” አሉ።
ማርቆስ 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 7:14-37
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች