የማርቆስ ወንጌል 6:21-43

የማርቆስ ወንጌል 6:21-43 አማ05

ሄሮድስ የተወለደበትን ቀን ለማክበር ለመንግሥት ባለሥልጣኖች፥ ለጦር ሹማምንትና ለአንዳንድ የታወቁ የገሊላ ነዋሪዎች ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ ይህም ለሄሮዲያዳ ጥሩ አጋጣሚ ሆነላት፤ ስለዚህም የሄሮዲያዳ ልጅ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገብታ እየጨፈረች ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ተጋባዦች አስደሰተች፤ ንጉሡም ልጅትዋን፦ “የምትፈልጊውን ማንኛውንም ነገር ጠይቂኝ፤ እሰጥሻለሁ” አላት፤ “የመንግሥቴንም እኩሌታ እንኳ ቢሆን፥ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ!” ሲል ማለላት። እርስዋም ወደ እናትዋ ሄዳ፥ “ምን ልጠይቅ?” አለቻት፤ እናትዋም “ ‘የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ይሰጠኝ፤’ ብለሽ ጠይቂ፤” አለቻት። ልጅትዋም ወዲያውኑ በፍጥነት ወደ ንጉሡ ተመልሳ፥ “የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ በሳሕን ሆኖ አሁን እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፤” ስትል ጠየቀች። ንጉሡ በዚህ ነገር በጣም አዘነ፤ ይሁን እንጂ በተጋባዦች ፊት ስላደረገው መሐላ የጠየቀችውን ሊከለክላት አልፈለገም። ስለዚህ ንጉሡ ወዲያውኑ አንዱን የዘብ ጠባቂ ወታደር የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ ላከው፤ ወታደሩም ወደ ወህኒው ቤት ሄዶ የዮሐንስን ራስ ቈረጠ፤ የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን አድርጎ አመጣና ለልጅትዋ ሰጣት፤ ልጅትዋም ለእናትዋ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይህን በሰሙ ጊዜ መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት። ሐዋርያት ከተላኩበት ተመልሰው መጥተው በኢየሱስ ፊት ተሰበሰቡ፤ ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። እርሱም “እናንተ ብቻችሁን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ ሂዱና ጥቂት ዕረፉ፤” አላቸው፤ ይህንንም ያለበት ምክንያት ወደ እነርሱ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ስለ ነበሩ ለመመገብ እንኳ ጊዜ ሊኖራቸው ስላልቻለ ነው። ስለዚህ ብቻቸውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍረው ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ፥ ሄዱ። ይሁን እንጂ እነርሱ ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቁአቸው፤ ከየከተማውም ወጥተው በእግር እየሮጡ ቀደሙአቸውና ወደ እነርሱ ተሰበሰቡ። ኢየሱስ ከጀልባው ሲወርድ ብዙ ሰዎችን አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በመሆናቸውም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። ጊዜው እየመሸ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ቦታው በረሓ ነው፤ ጊዜውም መሽቶአል፤ የሚበሉት የላቸውምና በአካባቢው ወዳሉት ገጠሮችና መንደሮች ሄደው ምግብ እንዲገዙ እነዚህን ሰዎች አሰናብታቸው።” ኢየሱስ ግን፦ “የሚበሉትን እናንተ ስጡአቸው” ሲል መለሰ። እነርሱም “ታዲያ፥ ሄደን የሚበሉትን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር ገዝተን እንስጣቸውን?” አሉ። እርሱም “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስቲ ሂዱና እዩ፤” አላቸው፤ አይተውም “አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አለ፤” አሉት። ኢየሱስም ሕዝቡን በቡድን ከፋፍለው፥ በለመለመው መስክ ላይ እንዲያስቀምጡአቸው ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። ስለዚህ ሕዝቡ በመቶና በኀምሳ ተከፋፍለው በቡድን ተቀመጡ። ኢየሱስም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አንሥቶ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ እንዲሁም ሁለቱን ዓሣ ለሁሉም አከፋፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ። ደቀ መዛሙርቱም የተረፈውን ቊርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ሰበሰቡ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች