በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምቱ፣ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ። የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሠኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናዪቱን፣ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት። ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፣ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሐላ ቃል ገባላት። እርሷም ወጥታ እናቷን፣ “ምን ልለምነው?” አለቻት። እናቷም፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ” አለቻት። ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው። ንጉሡ በነገሩ እጅግ ዐዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከርሱ ጋራ ስለ ነበሩ እንግዶች ሲል ቃሉን ለማጠፍ አልፈለገም። ወዲያውኑም ንጉሡ አንዱን ወታደር በፍጥነት ልኮ፣ የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ እርሱም ሄዶ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቈረጠ፤ በሳሕን አምጥቶ ለብላቴናዪቱ ሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን እንደ ሰሙ መጡ፤ ሬሳውንም ወስደው ቀበሩት። ሐዋርያትም በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው የሠሩትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለ ነበር ምግብ እንኳ ለመብላት ጊዜ ስላልነበራቸው፣ “እስኪ ብቻችሁን ከእኔ ጋራ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” አላቸው። ስለዚህ ብቻቸውን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄዱ። እነርሱም ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቋቸው፤ ከከተሞችም ሁሉ በእግር እየሮጡ ቀድመዋቸው ደረሱ። ኢየሱስ ከጀልባዋ በሚወርድበት ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩም ዐዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። በዚህ ጊዜ ቀኑ እየመሸ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቷል፤ በአካባቢው ሰው ወዳለበት መንደር ሄደው የሚበላ ነገር ገዝተው እንዲመገቡ ሕዝቡን አሰናብታቸው።” እርሱ ግን መልሶ፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “ሄደን በሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ገዝተን የሚበሉትን እንስጣቸውን?” አሉት። እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስኪ ሄዳችሁ እዩ” አላቸው። አይተውም፣ “ዐምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ” አሉት። ከዚያም፣ ሕዝቡን በለመለመ ሣር ላይ በቡድን በቡድን እንዲያስቀምጡ አዘዛቸው። ሕዝቡም መቶ መቶና ዐምሳ፣ ዐምሳ ሆነው በቡድን በቡድን ተቀመጡ። እርሱም ዐምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ በማየት ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ሁለቱንም ዓሣ ለሁሉም አካፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከተበላው እንጀራና ዓሣ፣ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ።
ማርቆስ 6 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 6:21-43
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች