“ሰው መብራትን አብርቶ በእንቅብ ውስጥ ወይም በአልጋ ሥር ያስቀምጠዋልን? የሚያስቀምጠው፥ ብርሃኑ በሚታይበት በመቅረዝ ላይ አይደለምን? እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረም ሳይታወቅ አይቀርም። እንግዲህ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምትሰሙት ነገር ተጠንቀቁ! በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ለእናንተም ይሰፈርላችኋል፤ በይበልጥም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ ዘር የሚዘራውን ሰው ትመስላለች። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀንም ይነቃል፤ እንዴት እንደ ሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድጋልም። ምድሪቱም በገዛ ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፥ ቀጥሎም ዛላውን ታሳያለች፤ በኋላም በዛላው ፍሬ ይገኛል። ሰብሉም በደረሰ ጊዜ መከር በመሆኑ ሰውየው ወዲያውኑ ማጭድ ያዘጋጃል።” ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር እናነጻጽራታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንገልጻታለን? የሰናፍጭን ዘር ትመስላለች፤ እርስዋ ስትዘራ በምድር ላይ ካለው ዘር ሁሉ ያነሰች ናት። ከተዘራች በኋላ ግን አድጋ ከአትክልት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በሥርዋ ጎጆ ሠርተው መጠለል እስኪችሉ ድረስ ታላላቅ ቅርንጫፎችን ታወጣለች።” ኢየሱስም ሰዎች ማስተዋል በሚችሉበት መጠን፥ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ቃሉን ይነግራቸው ነበር። ያለ ምሳሌም አያስተምራቸውም ነበር፤ ብቻቸውን ሲሆኑ ግን ሁሉን ነገር ለደቀ መዛሙርቱ ያስረዳቸው ነበር። በዚያኑ ቀን ማታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው። ከሕዝቡም ተለይተው ተሳፍሮበት በነበረው ጀልባ ኢየሱስን ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎችም ጀልባዎች አብረው ነበሩ። ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ተነሥቶ ውሃው በጀልባው እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ ጀልባውን ይመታ ጀመር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፥ በጀልባው በኋለኛው ክፍል ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ቀሰቀሱትና “መምህር ሆይ! ስንጠፋ አይገድህምን?” አሉት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም “ጸጥ በል!” አለው፤ ነፋሱ ተወ፤ ታላቅ ጸጥታም ሆነ። ኢየሱስም፦ “እንዲህ የምትፈሩት ለምንድን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም?” አላቸው። እነርሱም በጣም ፈርተው፥ እርስ በርሳቸው “ኧረ ለመሆኑ፥ ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።
የማርቆስ ወንጌል 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 4:21-41
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች