ማርቆስ 4:21-41

ማርቆስ 4:21-41 NASV

እንዲህም አላቸው፤ “መብራት ተወስዶ ከእንቅብ በታች ወይም ከዐልጋ ሥር ይቀመጣልን? የሚቀመጠው በመቅረዝ ላይ አይደለምን? ስለዚህ ተደብቆ የማይገለጥ፣ ተሸሽጎ ወደ ብርሃን የማይወጣ የለም፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።” በመቀጠልም፣ “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል። ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ላይ ግን፣ ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አላቸው። ከዚያም፣ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፤ ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ ምድርም ራሷ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ ዐጨዳ ይጀምራል።” ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋራ እናነጻጽራታለን? በምንስ ምሳሌ እንገልጻታለን? በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዕፀዋት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በትልልቅ ቅርንጫፎቿ ጥላ ሥር ያርፋሉ።” ኢየሱስም ሰዎች መረዳት በሚችሉበት መጠን፣ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ነገራቸው። ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ብቻ በሚሆኑበት ጊዜ ግን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያስረዳቸው ነበር። ያ ቀን በመሸ ጊዜ፣ “ወደ ማዶ እንሻገር” አላቸው። እነርሱ ሕዝቡን ትተው በጀልባዋ ውስጥ እንዳለ በዚያው ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም ዐብረውት ነበሩ። በዚህ ጊዜ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ተነሣ፤ ማዕበሉም ውሃ እስኪሞላት ድረስ ጀልባዋን ያናውጣት ነበር። ኢየሱስ ግን ትራስ ተንተርሶ ከጀልባዋ በስተኋላ በኩል ተኝቶ ነበር። እነርሱም ቀስቅሰውት፣ “መምህር ሆይ፤ ስንጠፋ አይገድድህምን?” አሉት። እርሱም ተነሥቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም፣ “ጸጥ፣ ረጭ በል!” አለው። ነፋሱም ጸጥ፣ ረጭ አለ፤ ፍጹምም ጸጥታ ሆነ። ደቀ መዛሙርቱንም፣ “ስለ ምን እንዲህ ፈራችሁ? እስከዚህ እምነት የላችሁምን?” አላቸው። እነርሱም በፍርሀት ተውጠው እርስ በርሳቸው፣ “ነፋሱም ሞገዱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች