የማርቆስ ወንጌል 14:51-72

የማርቆስ ወንጌል 14:51-72 አማ05

የበፍታ ነጠላ ብቻ የለበሰ አንድ ወጣት ግን ኢየሱስን ይከተል ነበር፤ ሰዎቹም በያዙት ጊዜ ነጠላውን ጥሎ ራቁቱን ሸሽቶ አመለጠ። ኢየሱስን ግን ወደ ካህናት አለቃው ቤት ወሰዱት፤ እዚያ የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና የሕግ መምህራን ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ የካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ይከተለው ነበር። እዚያም ከሎሌዎች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች ሁሉ፥ ኢየሱስን ለማስገደል ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ግን አላገኙም። ብዙዎችም በሐሰት መስክረውበት ነበር፤ ሆኖም የምስክርነት ቃላቸው ሳይስማማ ቀረ። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “እኔ ይህን በሰው እጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ ሌላ በሰው እጅ ያልተሠራ እሠራለሁ ብሎ ሲናገር ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ ምስክርነታቸው አልተስማማም። የካህናት አለቃውም በመካከላቸው ቆሞ፥ “ምንም አትመልስምን? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ የሚያቀርቡብህ ክስ ምንድን ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ እንጂ ምንም መልስ አልሰጠም። የካህናት አለቃውም “የቡሩክ እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ አንተ ነህን?” ሲል እንደገና ጠየቀው። ኢየሱስም “አዎ፥ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታያላችሁ! እንዲሁም በሰማይ ደመና ተመልሶ ሲመጣ ታያላችሁ” አለ። የካህናት አለቃውም በቊጣ ልብሱን ቀደደና “ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? እነሆ! ይህን የስድብ ቃል በእግዚአብሔር ላይ ሲሰነዝር ሰምታችኋል፤ ታዲያ ምን ይመስላችኋል?” አለ። ሁሉም በአንድ ቃል፥ “ሞት ይገባዋል!” ብለው ፈረዱበት። አንዳንዶችም ምራቃቸውን እንትፍ ይሉበት ጀመር፤ ዐይኑንም በጨርቅ ሸፍነው “አንተ ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደ መታህ ዕወቅ!” እያሉ በቡጢ ይመቱት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስ ከካህናት አለቃው ቤት በታች በግቢው ውስጥ እንዳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንድዋ መጣች፤ እርስዋ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኲር ብላ ተመለከተችውና “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ፤” አለችው። እርሱ ግን “እኔ አላውቅም፤ አንቺ የምትዪውም አይገባኝም፤” ሲል ካደ። ይህንንም ብሎ ወደ ደጃፉ እንደ ወጣ ዶሮ ጮኸ። ገረዲትዋም ጴጥሮስን አይታ፥ በዚያ ለቆሙት “ይህም ከእነርሱ ወገን ነው!” ስትል እንደገና ትናገር ጀመር፤ እርሱ ግን እንደገና ካደ። ጥቂት ቈየት ብሎም በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፥ “የገሊላ ሰው መሆንህን በእርግጥ አነጋገርህ ያስረዳል፤ ስለዚህ በእርግጥ አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤” አሉት። እርሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም!” እያለ ራሱን መራገምና መማል ጀመረ። ወዲያውኑ ዶሮ ሁለተኛ ጊዜ ጮኸ፤ ጴጥሮስም “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለውና ምርር ብሎ አለቀሰ።