ማርቆስ 14:51-72

ማርቆስ 14:51-72 NASV

ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ያገለደመ አንድ ወጣት ኢየሱስን ይከተል ነበር። ሰዎቹም ይህን ወጣት በያዙት ጊዜ፣ ግልድሙን ጥሎ ዕራቍቱን ሸሸ። ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፣ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከጠባቂዎቹ ጋራ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፣ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “ይህ፣ ‘የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ፣ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፣ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድን ነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደ ገና፣ “የቡሩኩ ልጅ፣ ክርስቶስ አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፣ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ። ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፣ እንዲህ አለ፤ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል? ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት። በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፣ “ትንቢት ተናገር!” ይሉት ነበር። ጠባቂዎቹም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ጴጥሮስ በግቢው ውስጥ በታችኛው በኩል ሳለ፣ ከሊቀ ካህናቱ የቤት ሠራተኞች አንዲቱ መጣች፤ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኵር ብላ ተመለከተችውና፣ “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋራ ነበርህ” አለችው። እርሱ ግን፣ “የምትዪውን እኔ ዐላውቀውም፤ አይገባኝምም” በማለት ካደ። ከዚያም ወደ መግቢያው በር ወጣ አለ፤ በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ። ሠራተኛዪቱም ባየችው ጊዜ እዚያ ለቆሙት፣ “ይህ ሰው ከእነርሱ አንዱ ነው” ብላ እንደ ገና ተናገረች። እርሱ ግን አሁንም ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፣ “የገሊላ ሰው እንደ መሆንህ መጠን፣ በርግጥ አንተ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት። እርሱ ግን፣ “እናንተ የምትሉትን ሰው እኔ አላውቀውም” እያለ ይምል ይገዘት ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስም፣ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው። ከዚያም ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።