የማርቆስ ወንጌል 13:1-13

የማርቆስ ወንጌል 13:1-13 አማ05

ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ሳለ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ “መምህር ሆይ! እነዚህን ድንጋዮችና ሕንጻዎች ተመልከት፤ የሚያስደንቁ ናቸው!” ኢየሱስም “እነዚህን ትልልቅ ሕንጻዎች ታያለህን? እነዚህ ድንጋዮች ሁሉ ይፈርሳሉ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ የሚቀር የለም፤” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብ፥ ዮሐንስና፥ እንድርያስ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “ይህ ነገር የሚሆነው መቼ ነው? ይህስ ሁሉ ሊፈጸም ሲቃረብ ምልክቱ ምንድን ነው? እስቲ ንገረን” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች ‘እኔ መሲሕ ነኝ!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙ ሰዎችንም ያሳስታሉ፤ በአቅራቢያችሁ ጦርነት ሲደረግና በሩቅም የጦርነትን ወሬ ስትሰሙ አትደንግጡ፤ ይህ ሁሉ ሊሆን ግድ ነው፤ ይሁን እንጂ መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ጦርነት ያነሣል፤ በየስፍራው የምድር መናወጥና ራብ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ እንደ ምጥ ጣር ያለ የጭንቅ መጀመሪያ ነው። “እናንተም ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ሰዎች ለፍርድ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በየምኲራቡም ይገርፉአችኋል፤ ምስክር እንድትሆኑኝ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ለፍርድ ትቆማላችሁ። ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ወንጌል ለዓለም ሕዝብ ሁሉ መዳረስ ይገባዋል። ሰዎች ይዘው ወደ ፍርድ ሲያቀርቡአችሁ፥ ‘ምን እንናገር ይሆን?’ በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁም። ስለዚህ በዚያን ሰዓት የሚሰጣችሁን ብቻ ተናገሩ። ወንድም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ በጠላትነት ይነሣሉ፤ ይገድሉአቸዋልም። ስለ ስሜ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች