ማርቆስ 13:1-13

ማርቆስ 13:1-13 NASV

ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “መምህር ሆይ፤ ድንጋዮቹ እንዴት እንደ ሆኑ፣ ሕንጻውም እንዴት ውብ እንደ ሆነ እይ!” አለው። ኢየሱስም መልሶ፣ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? አንዱ ድንጋይ በሌላው ላይ እንደ ሆነ አይቀርም፤ ሁሉም ፈራሽ ነው” አለው። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ትይዩ፣ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “ይህ መቼ እንደሚሆን ንገረን፤ የዚህስ ሁሉ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?” ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ እርሱ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ በምትሰሙበት ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህማ መሆን አለበት፤ ፍጻሜው ግን ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በብዙ ቦታም የመሬት መንቀጥቀጥና ራብ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። “ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ለአካባቢ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኵራቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ምስክር ትሆኑም ዘንድ በእኔ ምክንያት በገዦችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። አስቀድሞ ግን ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ መሰበክ አለበት። ይዘው ለፍርድ አሳልፈው በሚሰጧችሁ ጊዜ ሁሉ፣ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ እንጂ ምን እንናገራለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። “ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ይገድሏቸዋልም። ስለ ስሜ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች