የማርቆስ ወንጌል 12:18-27

የማርቆስ ወንጌል 12:18-27 አማ05

“የሙታን መነሣት የለም፤” የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ ኢየሱስ መጥተው፤ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፥ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሚስቱ በሞት ቢለይ ወንድሙ ሴትዮዋን አግብቶ ለሟቹ ዘር ይተካለት፤’ ብሎ ሙሴ ጽፎልናል። ታዲያ፥ ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የሁሉም ታላቅ ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሁለተኛውም ወንድሙ ያቺኑ ሴት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ ሆነ፤ በዚህ ሁኔታ ሰባቱም አግብተዋት ዘር ሳይተኩ ሞቱ፤ ከሁሉም በኋላ ደግሞ ሴትዮዋ ሞተች። ሰባቱም ወንድማማች በየተራ አግብተዋታልና እንግዲህ ሙታን በሚነሡበት ጊዜ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ባለማወቃችሁ አይደለምን? ሙታንስ ሲነሡ በሰማይ እንዳሉት መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም። ስለ ሙታን መነሣት የሆነ እንደ ሆነ ግን እግዚአብሔር ሙሴን ከቊጥቋጦው እሳት ውስጥ ምን እንደ ተናገረው ከሙሴ መጽሐፍ አላነበባችሁምን? ይኸውም ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤’ ያለው ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ እናንተ ግን እጅግ ትሳሳታላችሁ።”