ማርቆስ 12:18-27

ማርቆስ 12:18-27 NASV

ከዚህ በኋላ ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ የአንድ ሰው ወንድም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድሙ የሟችን ሚስት አግብቶ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል። ታዲያ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው አግብቷት ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሁለተኛውም ሴትዮዋን አገባት፤ እርሱም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ ሰባቱም አገቧት፤ ዘር ግን አልተኩም፤ በመጨረሻም ሴትዮዋ ሞተች። እንግዲህ፣ ሰባቱም አግብተዋታልና በትንሣኤ ለማንኛቸው ሚስት ልትሆን ነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታውቁ የምትስቱ አይደለምን? ሙታን በሚነሡበት ጊዜ እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም። ስለ ሙታን መነሣት ግን፣ በሙሴ መጽሐፍ ይኸውም ስለ ቍጥቋጦው በተነገረው ክፍል፣ እግዚአብሔር ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ያለውን አላነበባችሁምን? እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ እጅግ ተሳስታችኋል!”