ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን በምሳሌ እንዲህ ሲል ይነግራቸው ጀመር፦ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ዙሪያውንም ዐጠረ፤ የወይን መጭመቂያ የሚሆን ጒድጓድ ቆፍሮ አበጀ፤ ለወይኑ ጥበቃ የሚያገለግል ከፍተኛ የግንብ ማማ ሠራ፤ ከዚህም በኋላ የአትክልቱን ቦታ ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። ፍሬው በደረሰ ጊዜ፥ ከወይኑ ፍሬ እንዲያመጣለት አገልጋዩን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ይዘው ከደበደቡት በኋላ ባዶ እጁን ሰደዱት። እንደገና ባለቤቱ ሌላ አገልጋይ ላከ፤ ገበሬዎቹ ይህንንም በድንጋይ ፈንክተውና አዋርደው ሰደዱት። ቀጥሎም ሌላውን ቢልክ ገደሉት፤ እንዲሁም ብዙዎችን ቢልክ፥ አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ ሌሎቹንም ገደሉ። አሁን ማድረግ የቀረው የሚወደውን ልጁን መላክ ብቻ ነበር፤ ስለዚህ ‘ልጄንስ ያከብሩት ይሆናል’ ብሎ በማሰብ በመጨረሻ አንድ ልጁን ላከ። ነገር ግን ገበሬዎቹ እርስ በርሳቸው ‘ይህማ ወራሹ ነው! ኑ እንግደለው! ርስቱም ለእኛ ይሆናል’ ተባባሉ። ስለዚህ ልጁን ይዘው ገደሉት፤ ከወይኑ ተክልም ቦታ ውጪ ጣሉት። “እንግዲህ የወይኑ ተክል ጌታ ምን ያደርጋል? ባለቤቱ ራሱ ይመጣል፤ ገበሬዎቹንም ይገድላል፤ የወይኑንም ተክል ለሌሎች ይሰጣል። ለመሆኑ፥ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማእዘን ራስ ሆነ፤ ይህም የጌታ ሥራ ነው፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው።’ ” የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ቃል አላነበባችሁምን? የአይሁድ አለቆች ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ እነርሱን የሚመለከት መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈርተው ትተውት ሄዱ። ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን በንግግሩ ለማጥመድ ወደ እርሱ ተላኩ። ቀርበውም እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፥ አንተ እውነተኛ መሆንህን እናውቃለን፤ ሰውንም በመፍራትና በይሉኝታ የምታደርገው ነገር የለም፤ የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት ታስተምራለህ፤ ታዲያ፥ ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ሕጋዊ ነውን? ወይስ አይደለም? እንገብር ወይስ አንገብር?” ኢየሱስም ግብዝነታቸውን ዐውቆ፦ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ ገንዘቡን አምጡና አሳዩኝ፤” አላቸው። እነርሱም ገንዘቡን አመጡለት፤ እርሱም “በዚህ ገንዘብ ላይ ያለው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “የሮም ንጉሠ ነገሥት ነው፤” አሉት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ፤” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም በመልሱ ተደነቁ።
የማርቆስ ወንጌል 12 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 12:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos