የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 12:1-17

ማርቆስ 12:1-17 NASV

ከዚያም እንዲህ እያለ በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው ወይን ተከለ፤ ዙሪያውን ዐጠረ፤ ለመጭመቂያው ጕድጓድ ቈፈረ፤ የመጠበቂያም ማማ ሠራለት፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። በመከር ጊዜም ከወይኑ ፍሬ እንዲያመጣለት ከአገልጋዮቹ አንዱን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። እነርሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት። እንደ ገናም ሌላ አገልጋይ ላከ። እነርሱም ራሱን ፈንክተውና አዋርደው መለሱት። አሁንም እንደ ገና ሌላ ላከ፤ ይህኛውንም ገደሉት፤ ከሌሎች ከብዙዎቹ መካከል አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹንም ገደሉ። “አሁንም የሚላክ ሌላ ነበረው፤ እርሱም የሚወድደው ልጁ ነበረ፤ ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ በማለት ከሁሉ በኋላ ላከው። “ገበሬዎቹ ግን እርስ በርሳቸው፣ ‘ይህማ ዋናው ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለው፤ ርስቱ የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ፤ ከዚያም ይዘው ገደሉት፤ ከወይኑ ስፍራም አውጥተው ጣሉት። “እንግዲህ የወይኑ አትክልት ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይመጣል፤ ገበሬዎቹን ይገድላል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። እንዲህ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል አላነበባችሁምን፤ “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ፤ ጌታ ይህን አድርጓል፣ ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው’?” ምሳሌውን የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን ስላወቁ፣ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ስለ ፈሩ ትተውት ሄዱ። ከዚያም በነገር እንዲያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። እነርሱም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛ ሰው መሆንህን እናውቃለን፤ የሰዎች ማንነት ስለማይገድህም አታዳላም፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ብቻ በእውነት ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም? እኛስ እንክፈል ወይስ አንክፈል?” ኢየሱስ ግን ግብዝነታቸውን ዐውቆ፣ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር አምጡልኝና ልየው” አላቸው። እነርሱም አመጡለት፣ “ይህ የማን መልክ ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው፤ እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” አሉት። ኢየሱስም፣ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በእርሱ ተደነቁ።