በማግስቱም ከቢታንያ ሲመለሱ ኢየሱስ ተራበ። ቅጠልዋ የለመለመ የበለስ ዛፍም በሩቅ አይቶ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደ ሆነ በማለት ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ወደ እርስዋ በቀረበ ጊዜ በለስ የሚያፈራበት ወራት ስላልነበረ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ስለዚህ ኢየሱስ የበለስዋን ዛፍ፥ “ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ!” አላት። ይህንንም ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በውስጡ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ያስወጣ ጀመር፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ ማንም ሰው ምንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ እንዲተላለፍ አልፈቀደም። እንዲህም ሲል አስተማራቸው፤ “ ‘ቤቴ ለሕዝብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል!’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት።” የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ይህን ሲናገር ሰሙት፤ ሕዝቡም ሁሉ በትምህርቱ ይደነቁ ስለ ነበር ፈሩት፤ ስለዚህ እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ዘዴ ይፈልጉ ነበር። በመሸም ጊዜ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከከተማ ወጡ። በማግስቱ ማለዳ በመንገድ ሲያልፉ የበለሲቱ ዛፍ ከነስርዋ ደርቃ አዩአት። ጴጥሮስም ነገሩ ትዝ ብሎት ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ! እነሆ፥ የረገምሃት ዛፍ ደርቃለች” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ሰው በልቡ ሳይጠራጠር የሚፈልገው ነገር እንደሚፈጸምለት አምኖ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር፤’ ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ በጸሎት ማናቸውንም ነገር ብትለምኑ፥ እንደ ተፈጸመላችሁ አድርጋችሁ እመኑ፤ የምትለምኑትም ሁሉ ይሰጣችኋል። በሰማይ ያለው አባታችሁ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ እናንተም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ ሰው በአንዳች ነገር አስቀይሞአችሁ ከሆነ ይቅርታ አድርጉለት። እናንተ የሌሎችን በደል ይቅር ባትሉ ግን በሰማይ ያለው አባታችሁ የእናንተንም ኃጢአት ይቅር አይልላችሁም።” እንደገናም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲዘዋወር ሳለ የካህናት አለቆች፥ የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጡና “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ወይስ እነዚህን ነገሮች እንድታደርግ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተ መልስ ከሰጣችሁኝ፥ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። የዮሐንስ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ነበረ ወይስ ከሰው? እስቲ መልሱልኝ፤” አላቸው። እነርሱም “እንግዲህ ምን እንበል?” በማለት እርስ በርሳቸው ተመካከሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው፥’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰው ነው፥’ ብንልሳ?” ይህን እንዳይሉ ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን በእርግጥ ነቢይ ነው ይሉ ስለ ነበር ፈሩ። ስለዚህ “እኛ አናውቅም።” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም፤” አላቸው።
የማርቆስ ወንጌል 11 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 11:12-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos