የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 11:12-33

ማርቆስ 11:12-33 NASV

በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ። እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ከዚያም ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤ ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ። ሲያስተምራቸውም፣ “ ‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት!’” አላቸው። የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና። በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ። በማግስቱም ጧት በመንገድ ሲያልፉ፣ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ። ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምሃት በለስ ደርቃለች!” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “በእግዚአብሔር እመኑ፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና ይህንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል። ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደ ተቀበላችሁት አድርጋችሁ እመኑ፤ ይሆንላችሁማል። እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ፣ የሰማዩ አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲልላችሁ፣ እናንተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ። [ይቅር ባትሉ ግን የሰማዩ አባታችሁ በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።”] እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚዘዋወርበት ጊዜ፣ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀርበው፣ “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን እንድታደርግስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ!” እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ ‘ከሰማይ ነው’ ብንል፣ ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰው ነው’ ብንል …” ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ እውነተኛ ነቢይ እንደ ሆነ ይቈጥር ስለ ነበር ፈሩ። ስለዚህ ለኢየሱስ፣ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች