ሲያስተምርም፦ “ዘመኑ ተፈጽሞአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ! በወንጌልም እመኑ!” ይል ነበር። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። ኢየሱስም፦ “ኑ ተከተሉኝ፤ ዓሣን እንደምታጠምዱ ሁሉ ሰዎችንም እንድትሰበስቡልኝ አደርጋችኋለሁ፤” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ከዚያም ጥቂት አለፍ እንዳለ፥ ሌሎች ሁለት ወንድማማችን አየ፤ እነርሱም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ነበሩ፤ እነርሱ በጀልባ ላይ ሆነው መረባቸውን ይጠግኑ ነበር፤ ኢየሱስ ወዲያውኑ ጠራቸው፤ እነርሱም አባታቸውን ዘብዴዎስን ከሠራተኞቹ ጋር በጀልባው ላይ ትተውት ኢየሱስን ተከተሉት። አልፈውም ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ደረሱ፤ ወዲያው በሚቀጥለውም ሰንበት ኢየሱስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። ኢየሱስ፥ የሕግ መምህራን እንደሚያስተምሩት ዐይነት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለ ነበረ የሰሙት ሁሉ በትምህርቱ ተደነቁ። አንድ ርኩስ መንፈስ ያደረበት በምኲራባቸው የነበረ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? አንተ ማን እንደ ሆንክ እኔ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ።” ኢየሱስም ርኩሱን መንፈስ “ጸጥ ብለህ ከእርሱ ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን ጥሎ ካንፈራገጠው በኋላ በታላቅ ድምፅ እየጮኸ ከእርሱ ወጣ። “ይህ ምንድን ነው? ምን ዐይነት አዲስ ትምህርት ነው? ርኩሳን መናፍስትን እንኳ በሥልጣኑ ያዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤” እያሉ ሁሉም በመገረም እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ወዲያውኑ፥ የኢየሱስ ዝና በገሊላ ዙሪያ ባሉት አገሮች ሁሉ ተሰማ። በዚያኑ ጊዜ ኢየሱስ ከምኲራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና እንድርያስ ቤት ገባ። በቤት ውስጥ፥ የስምዖን ዐማት በንዳድ ሕመም አተኲሶአት ተኝታ ነበር፤ ስለ እርስዋም መታመም ወዲያው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም ወደ እርስዋ ቀረበና እጅዋን ይዞ አስነሣት፤ ትኲሳቱም ወዲያው ለቀቃት፤ ተነሥታም አስተናገደቻቸው። ፀሐይ ጠልቃ በመሸ ጊዜ ሰዎች በሽተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ ኢየሱስ አመጡ። የከተማው ሰዎች ሁሉ በደጅ ተሰብስበው ነበር። ኢየሱስ በልዩ ልዩ በሽታ የሚሠቃዩትን ብዙ ሰዎች ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትንም አስወጣ፤ አጋንንቱም እርሱ ማን እንደ ሆነ ያውቁ ነበር፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም።
የማርቆስ ወንጌል 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 1:15-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos