የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 1:15-34

ማርቆስ 1:15-34 NASV

“ጊዜው ደርሷል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ!” እያለ ይሰብክ ነበር። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ፣ መረብ ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። ኢየሱስም፣ “ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ትንሽ ዕልፍ እንዳለ፣ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በጀልባ ሆነው መረባቸውን ሲያበጃጁ አያቸውና፣ ወዲያውኑ ጠራቸው። እነርሱም አባታቸውን በጀልባው ላይ ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋራ ትተው ተከተሉት። ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። እንደ ጸሐፍት ሳይሆን፣ እንደ ባለሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ። በዚያ ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” ኢየሱስም፣ “ጸጥ በል፤ ከርሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኀይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ከርሱ ወጣ። ሁሉም በመገረም፣ “ይህ ሥልጣን ያለው አዲስ ትምህርት ምንድን ነው? ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል!” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ። ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ወጣ። ወዲያው ከምኵራብ እንደ ወጡ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋራ ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገቡ። የስምዖን ዐማት በትኵሳት በሽታ ታምማ ተኝታ ነበር፤ ስለ እርሷም ነገሩት፤ ስለዚህም እርሱ ወደ ተኛችበት በመሄድ እጇን ይዞ አስነሣት፤ ትኵሳቱም ተዋት፤ ተነሥታም ታገለግላቸው ጀመር። ጀንበር ከጠለቀች በኋላ፣ ምሽት ላይ የአካባቢው ሰዎች ሕመምተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ። የከተማዋ ሕዝብ በሙሉ በቤቱ ደጅ ላይ ተሰብስቦ ነበር። እርሱም በተለያየ በሽታ የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትም አወጣ፤ ነገር ግን አጋንንቱ የኢየሱስን ማንነት ያውቁ ስለ ነበር እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች