የማቴዎስ ወንጌል 9:1-13

የማቴዎስ ወንጌል 9:1-13 አማ05

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጀልባ በመሳፈር ባሕሩን ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ መጣ። በዚያም ሰዎች በአልጋ ላይ የተኛ አንድ ሽባ ይዘው ወደ እርሱ መጡ። እርሱም እምነታቸውን አይቶ፥ ሽባውን፥ “ልጄ ሆይ! አይዞህ፤ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ አንዳንድ የሕግ መምህራን፥ “ይህ ሰው በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ይናገራል!” እያሉ በልባቸው አሰቡ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምን ይህን ክፉ ነገር በልባችሁ ታስባላችሁ? ለመሆኑ ‘ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ!’ ከማለት የትኛው ይቀላል? ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ” ሽባውን ሰው “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። ሰውዬውም ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተገረሙ፤ እንዲህ ያለውንም ሥልጣን ለሰው በመስጠቱ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ኢየሱስ ከዚያ ቦታ ተነሥቶ ሲሄድ ሳለ ማቴዎስ የተባለውን ቀራጭ በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ!” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው። ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች፥ ወደዚያ መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማእድ ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም ይህን አይተው ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ስለምን አብሮ ይበላል?” አሉአቸው። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም። ሂዱ፤ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ ተብሎ የተጻፈው ምን ማለት እንደ ሆነ መርምራችሁ አስተውሉ። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ ለመጥራት ነው” አላቸው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች