ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሰዎች ይዩልን ብላችሁ መልካም ሥራችሁን በሰዎች ፊት ከማድረግ ተጠንቀቁ፤ አለበለዚያ ግን፥ በሰማይ አባታችሁ ዘንድ ምንም ዋጋ አታገኙም። ስለዚህ ለድኾች ምጽዋት በምትመጸውትበት ጊዜ፥ ግብዞች በየምኲራቡና በየመንገዱ እንደሚያደርጉት ለታይታ አታድርጉ፤ በእውነት እነግራችኋለሁ፥ እነርሱ ዋጋቸውን አስቀድመው አግኝተዋል። አንተ ግን ምጽዋት ስትመጸውት ቀኝ እጅህ የሚያደርገውን ግራ እጅህ አይወቅ። እንግዲህ ምጽዋትህ በስውር ይሁን፤ በስውር የተሠራውን የሚያየው አባትህ፥ የመልካም ሥራህን ዋጋ ይከፍልሃል። “በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ! እነርሱ ሰው እንዲያይላቸው ብለው በየምኲራቡና በየመንገዱ ዳር ቆመው መጸለይ ይወዳሉ። በእውነት እላችኋለሁ፥ እነርሱ ዋጋቸውን በቅድሚያ አግኝተዋል። አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ ክፍልህ ገብተህ፥ በርህን ዝጋና በስውር ወዳለው ወደማይታይ አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተሠራውን የሚያይ አባትህም የመልካም ሥራህን ዋጋ ይከፍልሃል። “እናንተ ስትጸልዩ እንደ አሕዛብ ከንቱ ቃል በመደጋገም አትለፍልፉ፤ እነርሱ በመደጋገማቸው ብዛት እግዚአብሔር ጸሎታቸውን የሚሰማቸው ይመስላቸዋል። እናንተ ግን፥ አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ነገር ገና ሳትለምኑት አስቀድሞ ስለሚያውቅ እንደ እነርሱ አትሁኑ። ስለዚህ እናንተ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፦ ‘በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ! ስምህ ይመስገን፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነ፥ እንዲሁም በምድር ይሁን። የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን። እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል፥ በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉ አድነን እንጂ፥ ወደ ፈተና አታግባን፤ [መንግሥት፥ ኀይልና ክብር ለዘለዓለም ያንተ ነው፤ አሜን።’] “የሰዎችን በደል ይቅር ብትሉላቸው፥ እናንተንም የሰማዩ አባታችሁ ይቅር ይልላችኋል። የሰዎችን በደል ይቅር ባትሉላቸው ግን የእናንተንም በደል የሰማዩ አባታችሁ ይቅር አይልላችሁም።” ኢየሱስም ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “በምትጾሙበት ጊዜ፥ መጾማቸውን ሰዎች እንዲያውቁላቸው፥ ፊታቸውን እንደሚለውጡት እንደ ግብዞች፥ ፊታችሁን አታጠውልጉ፤ በእውነት እላችኋለሁ፥ እነርሱ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ በዚህ አኳኋን፥ መጾምህን በስውር ካለው አባትህ በቀር ሌላ ማንም አያውቅም። በስውር የተሠራውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።”
የማቴዎስ ወንጌል 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 6:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos