የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 6

6
ስለ ምጽዋት አሰጣጥ
1ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሰዎች ይዩልን ብላችሁ መልካም ሥራችሁን በሰዎች ፊት ከማድረግ ተጠንቀቁ፤ አለበለዚያ ግን፥ በሰማይ አባታችሁ ዘንድ ምንም ዋጋ አታገኙም። #ማቴ. 23፥5። 2ስለዚህ ለድኾች ምጽዋት በምትመጸውትበት ጊዜ፥ ግብዞች በየምኲራቡና በየመንገዱ እንደሚያደርጉት ለታይታ አታድርጉ፤ በእውነት እነግራችኋለሁ፥ እነርሱ ዋጋቸውን አስቀድመው አግኝተዋል። 3አንተ ግን ምጽዋት ስትመጸውት ቀኝ እጅህ የሚያደርገውን ግራ እጅህ አይወቅ። 4እንግዲህ ምጽዋትህ በስውር ይሁን፤ በስውር የተሠራውን የሚያየው አባትህ፥ የመልካም ሥራህን ዋጋ ይከፍልሃል።
ስለ ጸሎት
(ሉቃ. 11፥2-4)
5“በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ! እነርሱ ሰው እንዲያይላቸው ብለው በየምኲራቡና በየመንገዱ ዳር ቆመው መጸለይ ይወዳሉ። በእውነት እላችኋለሁ፥ እነርሱ ዋጋቸውን በቅድሚያ አግኝተዋል። #ሉቃ. 18፥10-14። 6አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ ክፍልህ ገብተህ፥ በርህን ዝጋና በስውር ወዳለው ወደማይታይ አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተሠራውን የሚያይ አባትህም የመልካም ሥራህን ዋጋ ይከፍልሃል።
7“እናንተ ስትጸልዩ እንደ አሕዛብ ከንቱ ቃል በመደጋገም አትለፍልፉ፤ እነርሱ በመደጋገማቸው ብዛት እግዚአብሔር ጸሎታቸውን የሚሰማቸው ይመስላቸዋል። #1ነገ. 18፥25-29። 8እናንተ ግን፥ አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ነገር ገና ሳትለምኑት አስቀድሞ ስለሚያውቅ እንደ እነርሱ አትሁኑ። 9ስለዚህ እናንተ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፦
‘በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ!
ስምህ ይመስገን፤
10መንግሥትህ ትምጣ፤
ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነ፥
እንዲሁም በምድር ይሁን።
11የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን።
12እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል፥
በደላችንን ይቅር በለን፤
13ከክፉ አድነን እንጂ፥
ወደ ፈተና አታግባን፤
[መንግሥት፥ ኀይልና ክብር
ለዘለዓለም ያንተ ነው፤
አሜን።’]
14“የሰዎችን በደል ይቅር ብትሉላቸው፥ እናንተንም የሰማዩ አባታችሁ ይቅር ይልላችኋል። 15የሰዎችን በደል ይቅር ባትሉላቸው ግን የእናንተንም በደል የሰማዩ አባታችሁ ይቅር አይልላችሁም።” #ማቴ. 11፥25-26።
ስለ ጾም
16ኢየሱስም ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “በምትጾሙበት ጊዜ፥ መጾማቸውን ሰዎች እንዲያውቁላቸው፥ ፊታቸውን እንደሚለውጡት እንደ ግብዞች፥ ፊታችሁን አታጠውልጉ፤ በእውነት እላችኋለሁ፥ እነርሱ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። #ኢሳ. 58፥5። 17አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ 18በዚህ አኳኋን፥ መጾምህን በስውር ካለው አባትህ በቀር ሌላ ማንም አያውቅም። በስውር የተሠራውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።”
በምድር ላይ ሀብት ማከማቸት እንደማይገባ ማስተማሩ
(ሉቃ. 12፥33-34)
19ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ብልና ዝገት በሚያጠፉበት፥ ሌቦችም ሰብረው በሚሰርቁበት፥ በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። #ያዕ. 5፥2-3። 20ይልቅስ ብልና ዝገት ሊያጠፉት በማይችሉበት፥ ሌቦችም ሰብረው በማይሰርቁበት በሰማይ ሀብታችሁን አከማቹ። 21ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይገኛል።
የሰውነት መብራት
(ሉቃ. 11፥34-36)
22“ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ፥ ሰውነትህ በሙሉ ብርሃን ይሆናል፤ 23ዐይንህ ጤናማ ካልሆነ ግን፥ ሰውነትህ በሙሉ ጨለማ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማው እንዴት የባሰ ይሆን!
ስለ ኑሮ መጨነቅ የማይገባ መሆኑ
(ሉቃ. 16፥1312፥22-31)
24“አንድ ሰው ለሁለት ጌቶች አገልጋይ ሊሆን አይችልም፤ ወይም አንዱን ይጠላል፥ ሌላውንም ይወዳል፤ ወይም አንዱን ያከብራል፥ ሌላውን ይንቃል፤ እንዲሁም አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ አገልጋይ መሆን አይችልም። 25ስለዚህ እንዲህ እላችኋለሁ፤ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ በማለት ስለ ኑሮአችሁ አትጨነቁ፤ ከምግብ ሕይወት፥ ከልብስም ሰውነት አይበልጥምን? 26እስቲ በሰማይ ላይ ወደሚበሩት ወፎች ተመልከቱ፤ እነርሱ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራ አይከቱም፤ ነገር ግን የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? 27ለመሆኑ ከእናንተ በመጨነቅ፥ በዕድሜው ላይ አንድ ቀን እንኳ መጨመር የሚችል ማን ነው? #6፥27 በዕድሜው ላይ አንድ ቀን፦ በአንዳንድ ትርጒሞች “በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ” የሚል ይገኛል። #መዝ. 39፥5-7። 28ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የአሸንድዬ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ እስቲ ተመልከቱ፤ እነርሱ በሥራ አይደክሙም፤ አይፈትሉም፤ 29ነገር ግን ሰሎሞንስ እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ፥ ከእነርሱ እንደ አንዲቱ አለበሰም እላችኋለሁ። #1ነገ. 10፥4-7፤ 2ዜ.መ. 9፥3-6። 30ታዲያ ዛሬ ታይቶ ነገ በእሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር፥ እግዚአብሔር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ! እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም! 31ስለዚህ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ እያላችሁ በማሰብ አትጨነቁ። 32ይህን ለማግኘትማ አሕዛብም ይፈልጋሉ፤ እናንተ ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ፥ የሰማይ አባታችሁ ያውቃል። 33እናንተ ግን፥ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፤ የቀረው ነገር ሁሉ ይጨመርላችኋል፤ 34ነገ ለራሱ ይጨነቃል፤ ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማቴዎስ ወንጌል 6