የማቴዎስ ወንጌል 5:17-30

የማቴዎስ ወንጌል 5:17-30 አማ05

ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የኦሪትን ሕግና የነቢያትን ትምህርት ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ እኔ እንዲፈጸሙ ላደርጋቸው መጣሁ እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም። በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ጭረት ወይም አንዲት ነጥብ አትሻርም። ስለዚህ ከእነዚህ ትእዛዞች አነስተኛ የሆነችውን አንድዋን እንኳ የሚያፈርስና ሌሎችም ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው በመንግሥተ ሰማይ አነስተኛ ይሆናል። ነገር ግን ትእዛዞችን ሁሉ የሚፈጽምና ሌሎችም ሰዎች እንዲሁ እንዲፈጽሙ የሚያስተምር ሰው በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል። ስለዚህ የእናንተ ጽድቅ ከሕግ መምህራንና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደማትገቡ እነግራችኋለሁ። “በቀድሞ ጊዜ ለነበሩ ሰዎች የተባለውን ሰምታችኋል፤ ይኸውም ‘አትግደል፤ ሰውን የገደለ ይፈረድበታል’ የሚል ነው። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ የሚቈጣ ሁሉ ይፈረድበታል፤ ደግሞም ወንድሙን፥ ‘አንተ የማትረባ!’ ብሎ የሚሳደብ በሸንጎ ይፈረድበታል፤ ‘ደደብ!’ ብሎ የሚሳደብ ሁሉ በገሃነመ እሳት ይፈረድበታል። ስለዚህ አንተ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ፥ ያዘነብህ ወንድም መኖሩን ብታስታውስ፥ መባህን በመሠዊያው ፊት አስቀምጥና፥ ሄደህ በመጀመሪያ ከዚያ ከወንድም ጋር ታረቅ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰህ መባህን አቅርብ። ባላጋራህ ከሶህ ከእርሱ ጋር ወደ ፍርድ ቤት ስትሄድ በመንገድ ላይ ሳለህ ቶሎ ብለህ ከባላጋራህ ጋር ተስማማ። አለበለዚያ ባላጋራህ ለዳኛ፥ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ ይሰጥህና ወደ ወህኒ ቤት ትገባለህ። በእውነት እልሃለሁ፥ የተፈረደብህን የመጨረሻዋን ሳንቲም ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘አታመንዝር!’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ‘ሴትን ተመልክቶ የተመኛት ሁሉ፥ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመነዘረ’ እላችኋለሁ። የቀኝ ዐይንህ ለኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ አውጥተህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ ቈርጠህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች