“ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳ አትሻርም። ስለዚህ ማንም ከእነዚህ ትእዛዞች አነስተኛዪቱን እንኳ ቢተላለፍ፣ ሌሎችንም እንዲተላለፉ ቢያስተምር፣ በመንግሥተ ሰማይ ታናሽ ተብሎ ይጠራል፤ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዞች እየፈጸመ ሌሎችም እንዲፈጽሙ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይባላል። ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከኦሪት ሕግ መምህራን ጽድቅ ልቆ ካልተገኘ መንግሥተ ሰማይ መግባት አትችሉም። “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቈጣ ይፈረድበታል፤ ማንም ወንድሙን ‘ጅል’ የሚል በሸንጎ ፊት ይጠየቅበታል፤ ‘ደደብ’ የሚለው ደግሞ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይጠብቀዋል። “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ፣ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣ መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋራ ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ። “የከሰሰህ ባላጋራህ እንዳያስፈርድብህ፣ ዳኛውም ለአገልጋዩ አሳልፎ እንዳይሰጥህ፣ ወደ ወህኒ እንዳትጣል፣ በመንገድ ላይ ሳለህ ከባላጋራህ ጋራ ፈጥነህ ተስማማ። እውነት እልሃለሁ፤ ካስፈረደብህ ግን የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም። “ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዐይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከርሷ ጋራ አመንዝሯል። ቀኝ ዐይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።
ማቴዎስ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 5:17-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች