የማቴዎስ ወንጌል 18:12-35

የማቴዎስ ወንጌል 18:12-35 አማ05

ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እስቲ ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን አንዱን ለመፈለግ አይሄድምን? እውነት እላችኋለሁ፤ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ በተገኘው በግ ደስ ይለዋል። እንዲሁም በሰማይ ያለው አባታችሁ ከነዚህ ከታናናሾች አንዱም እንዲጠፋ አይፈልግም። “ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ በደሉን ንገረው፤ ቢሰማህ እንደገና ወንድምህ እንዲሆን ታደርገዋለህ፤ ባይሰማህ ግን የሁለት ወይም የሦስት ሰዎች ምስክርነት ስለሚጸና ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ይዘህ ወደ እርሱ ሂድ። እነርሱንም አልሰማም ቢል ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም የማይሰማ ከሆነ እንደ አረመኔና ተጸጽቶ እንደማይመለስ ኃጢአተኛ ቊጠረው። “በእውነት እላችኋለሁ፤ በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱትም በሰማይ የተፈታ ይሆናል። ደግሞም እላችኋለሁ፤ ከእናንተ ሁለቱ በምድር ላይ ማናቸውንም ነገር ለመለመን ተስማምተው ቢጸልዩ፥ በሰማይ ያለው አባቴ ይፈጽምላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት ስፍራ እኔ በመካከላቸው እገኛለሁ።” በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፦ “ጌታ ሆይ! ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም፤ ስለዚህ መንግሥተ ሰማይ ከአገልጋዮቹ ጋር ሊተሳሰብ የፈለገውን ንጉሥ ትመስላለች፤ ንጉሡ መተሳሰብ በጀመረ ጊዜ በብዙ ሺህ መክሊት የሚቈጠር ዕዳ ያለበት አንድ አገልጋይ ተይዞ መጣ። ይህ አገልጋይ ዕዳውን መክፈል ስላልቻለ እርሱም፥ ሚስቱም፥ ልጆቹም፥ ያለውም ንብረት ሁሉ ተሸጦ ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። አገልጋዩ ግን በጌታው እግር ሥር ተንበርክኮ ‘ጌታ ሆይ! እባክህ ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ!’ ሲል ለመነው። ጌታውም ራራለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ተወለት። “ነገር ግን ያ አገልጋይ ከዚያ ወጥቶ ሲሄድ ሳለ መቶ ዲናር ያበደረውን የሥራ ጓደኛውን አገኘና አንገቱን አንቆ ይዞ፥ ‘ያበደርኩህን ገንዘብ ክፈለኝ!’ አለው። አገልጋይ ጓደኛውም በእግሩ ሥር ወድቆ፥ ‘እባክህ ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ!’ ሲል ለመነው። ሰውየው ግን እምቢ አለው። እንዲያውም ይዞት ሄደና ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወህኒ ቤት አሳሰረው። እንደርሱ ያሉ ሌሎች የሥራ ጓደኞቹ ይህን ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት። ጌትዮውም ያን አገልጋይ አስጠርቶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ አገልጋይ! ስለ ለመንከኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውኩልህ፤ ታዲያ፥ እኔ ዕዳህን እንደ ተውኩልህ፥ አንተስ ባልንጀራህ ለሆነው አገልጋይ ዕዳውን ልትተውለት አይገባህም ነበርን?’ ስለዚህ ጌታው ተቈጥቶ ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለወህኒ ቤቱ ኀላፊዎች አሳልፎ ሰጠው። “እንግዲህ እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልብ ይቅር ባትሉ በሰማይ ያለው አባቴም እንዲሁ ያደርግባችኋል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች