የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 18:12-35

ማቴዎስ 18:12-35 NASV

“እስኪ ንገሩኝ፤ አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት፣ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ለመፈለግ አይሄድምን? እውነት እላችኋለሁ፤ የጠፋውን በግ ሲያገኝ፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በዚያ በተገኘው ደስ ይለዋል። እንደዚሁም ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱ እንኳ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም። “ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን እንደ ገና የራስህ ታደርገዋለህ። ባይሰማህ ግን፣ ነገር ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች አፍ ስለሚጸና፣ አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ አነጋግረው። እነርሱን ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማ፣ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ ቍጠረው። “እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር ያሰራችሁት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታችሁት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል። “ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር ላይ ሁለት ሆናችሁ ስለ ምንም ነገር በመስማማት ብትጠይቁ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላችኋል፤ ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት መካከል በዚያ እገኛለሁና።” በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው። ኢየሱስም “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” አለው። “ስለዚህ መንግሥተ ሰማይ፣ በባሪያዎቹ እጅ የነበረውን ሒሳብ ለመተሳሰብ የፈለገን ንጉሥ ትመስላለች። ሒሳቡን ማጣራት እንደ ጀመረም ዐሥር ሺሕ ታላንት ዕዳ ያለበትን አንድ አገልጋይ አቀረቡለት። አገልጋዩም ያለበትን ዕዳ መክፈል ስላቃተው እርሱ ራሱ፣ ሚስቱ፣ ልጆቹና ንብረቱ ሁሉ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። “በዚህ ጊዜ ባሪያው እግሩ ላይ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው። ጌታውም ዐዘነለትና ባሪያውን ማረው፤ ዕዳውንም ትቶለት አሰናበተው። “ያ ባሪያ ከጌታው ፊት እንደ ወጣ አንድ መቶ ዲናር የርሱ ዕዳ ያለበትን አገልጋይ ባልንጀራውን አግኝቶ ዕንቅ አድርጎ በመያዝ፣ ‘ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ!’ አለው። “ባልንጀራው አገልጋይም ከፊቱ ወድቆ፣ ‘ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ለመነው። “ነገር ግን ሊታገሠው ፈቃደኛ ስላልነበረ፣ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍለው ድረስ ወህኒ ቤት አስገባው። የሆነውን ነገር ያዩ ሌሎች አገልጋዮችም በጣም ዐዘኑ፤ ሄደውም ሁኔታውን በሙሉ ለጌታቸው ነገሩት። “በዚህ ጊዜ ጌታው ባሪያውን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፤ ስለ ለመንኸኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ አንተም ባልንጀራህን ልትምረው አይገባህም ነበርን?’ በቍጣም ያለበትን ዕዳ ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ ለአሳሪዎች አሳልፎ ሰጠው። “ስለዚህ እያንዳንዳችሁ ወንድሞቻችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ፣ የሰማዩ አባቴም እንደዚሁ ያደርግባችኋል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች