የማቴዎስ ወንጌል 18:1-20

የማቴዎስ ወንጌል 18:1-20 አማ05

በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም አንድ ሕፃን ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ፤ እንዲህም አለ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፦ ካልተለወጣችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም። እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል። እንደዚህ ያለውን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል። “ማንም ሰው በእኔ ከሚያምኑት ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያስት ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢጣልና ቢሰጥም ይሻለዋል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሰዎች እንዲሰናከሉ በሚያደርጉት ነገሮች ምክንያት ለዓለም ወዮላት! መቼም የሚያሰናክሉ ነገሮች መምጣታቸው አይቀርም፤ ነገር ግን የመሰናከያው መምጫ ለሚሆነው ለዚያ ሰው ወዮለት! ስለዚህ እጅህ ወይም እግርህ ኃጢአት እንድትሠራ ቢያስትህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው! ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘለዓለም እሳት ከምትጣል ይልቅ ጒንድሽ ወይም አንካሳ ሆነህ ወደ ዘለዓለም ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ዐይንህም ኃጢአት እንድትሠራ ቢያስትህ አውጥተህ ወዲያ ጣለው! ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ ዘለዓለም ሕይወት መግባት ይሻልሃል። በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው ዘወትር በሰማይ ያለውን ያባቴን ፊት ስለሚያዩ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ። [ የሰው ልጅም የመጣው የጠፋውን ለማዳን ነው።”] ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እስቲ ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን አንዱን ለመፈለግ አይሄድምን? እውነት እላችኋለሁ፤ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ በተገኘው በግ ደስ ይለዋል። እንዲሁም በሰማይ ያለው አባታችሁ ከነዚህ ከታናናሾች አንዱም እንዲጠፋ አይፈልግም። “ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ በደሉን ንገረው፤ ቢሰማህ እንደገና ወንድምህ እንዲሆን ታደርገዋለህ፤ ባይሰማህ ግን የሁለት ወይም የሦስት ሰዎች ምስክርነት ስለሚጸና ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ይዘህ ወደ እርሱ ሂድ። እነርሱንም አልሰማም ቢል ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም የማይሰማ ከሆነ እንደ አረመኔና ተጸጽቶ እንደማይመለስ ኃጢአተኛ ቊጠረው። “በእውነት እላችኋለሁ፤ በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱትም በሰማይ የተፈታ ይሆናል። ደግሞም እላችኋለሁ፤ ከእናንተ ሁለቱ በምድር ላይ ማናቸውንም ነገር ለመለመን ተስማምተው ቢጸልዩ፥ በሰማይ ያለው አባቴ ይፈጽምላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት ስፍራ እኔ በመካከላቸው እገኛለሁ።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች