በዚያ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ አንድ ሕፃን ወደ ራሱ ጠርቶ በመካከላቸው አቆመና እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ካልተለወጣችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም። ስለዚህ በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ፣ እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው። ማንም እንደዚህ ያለውን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል። “ነገር ግን ማንም በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያሰናክል፣ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥሎ ቢሰጥም ይሻለዋል። ይህች ዓለም የመሰናክል ምክንያት በመሆኗ ወዮላት! መሰናክል መምጣቱ አይቀርምና፤ ነገር ግን የመሰናክሉ ምክንያት ለሚሆነው ሰው ወዮለት! እጅህ ወይም እግርህ ለመሰናክል ምክንያት ቢሆንብህ፣ ቈርጠህ ጣለው፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል፣ ዐንካሳ ወይም ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። እንዲሁም ዐይንህ ለመሰናክል ምክንያት ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። “ከእነዚህ ከታናናሾች መካከል አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ እላችኋለሁና፤ በሰማይ ያሉት መላእክታቸው በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ሁልጊዜ ያያሉ፤ [ምክንያቱም የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ነው።] “እስኪ ንገሩኝ፤ አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት፣ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ለመፈለግ አይሄድምን? እውነት እላችኋለሁ፤ የጠፋውን በግ ሲያገኝ፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በዚያ በተገኘው ደስ ይለዋል። እንደዚሁም ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱ እንኳ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም። “ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን እንደ ገና የራስህ ታደርገዋለህ። ባይሰማህ ግን፣ ነገር ሁሉ በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች አፍ ስለሚጸና፣ አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ አነጋግረው። እነርሱን ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም ባይሰማ፣ እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ ቍጠረው። “እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር ያሰራችሁት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታችሁት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል። “ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር ላይ ሁለት ሆናችሁ ስለ ምንም ነገር በመስማማት ብትጠይቁ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላችኋል፤ ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት መካከል በዚያ እገኛለሁና።”
ማቴዎስ 18 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 18
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 18:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች