የማቴዎስ ወንጌል 14:8-21

የማቴዎስ ወንጌል 14:8-21 አማ05

እርስዋም በእናቷ ተመክራ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በሳሕን አሁኑኑ ስጠኝ!” አለችው። ንጉሡ በዚህ ነገር አዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር በማእድ ተቀምጠው ስለ ነበሩት ሰዎች ይሉኝታ ብሎ የዮሐንስ ራስ እንዲሰጣት አዘዘ። ስለዚህ ወደ ወህኒ ቤት ሰው ልኮ የዮሐንስን ራስ በወህኒ ቤት አስቈረጠ። የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን አምጥተው ለልጅቱ ሰጡአት፤ እርስዋም ለእናትዋ ወስዳ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት፤ ሄደውም ይህን ነገር ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስ የዮሐንስን መሞት በሰማ ጊዜ በጀልባ ተሳፈረና ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ብቻውን ለመሆን ሄደ። ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ከየከተማው እየወጡ በእግር ተከተሉት። ኢየሱስ ከጀልባው በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብን አይቶ ራራላቸው፤ በሽተኞቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቶአል፤ ስለዚህ ሕዝቡ በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች ሄደው ምግባቸውን እንዲገዙ አሰናብታቸው” አሉት። ኢየሱስ ግን፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ እነርሱ እንዲሁ ሊሄዱ አይገባም!” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “እኛ እዚህ ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው” አሉት። ኢየሱስም “እነርሱኑ ወደ እኔ አምጡልኝ!” አላቸው። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ በመስኩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አንሥቶ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ እንጀራውንም ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ዐደሉ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውን ፍርፋሪ፥ ደቀ መዛሙርቱ በዐሥራ ሁለት መሶብ ሞልተው አነሡ። የበሉትም ሰዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አምስት ሺህ ያኽል ወንዶች ነበሩ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች