የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 14:1-21

የማቴዎስ ወንጌል 14:1-21 አማ05

በዚያን ጊዜ የገሊላ ክፍለ ሀገር ገዢ የነበረው ሄሮድስ፥ የኢየሱስን ዝና ሰማ። አገልጋዮቹን፥ “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤ እነዚህ ድንቅ ነገሮች በእርሱ አማካይነት የሚደረጉት ስለዚህ ነው” አላቸው። ሄሮድስ ዮሐንስን አስይዞ በወህኒ ቤት አሳስሮት ነበር፤ ይህንንም ያደረገው የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት በነበረችው በሄሮዲያዳ ምክንያት ነው። ዮሐንስ ለሄሮድስ፦ “የወንድምህን ሚስት እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም!” ብሎት ነበር። ስለዚህ ሄሮድስ ዮሐንስን ሊገድለው ይፈልግ ነበር፤ ነገር ግን የአይሁድ ሕዝብ እንደ ነቢይ ያዩት ስለ ነበር ሕዝቡን ፈራ። የሄሮድስ ልደት በሚከበርበት ቀን የሄሮድያዳ ልጅ መጥታ በተጋባዦች መካከል እየጨፈረች ሄሮድስን አስደሰተች። ስለዚህም ሄሮድስ፦ “የምትፈልጊውን ነገር ጠይቂኝ! እኔም እሰጥሻለሁ!” ሲል በመሐላ ቃል ገባላት። እርስዋም በእናቷ ተመክራ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በሳሕን አሁኑኑ ስጠኝ!” አለችው። ንጉሡ በዚህ ነገር አዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር በማእድ ተቀምጠው ስለ ነበሩት ሰዎች ይሉኝታ ብሎ የዮሐንስ ራስ እንዲሰጣት አዘዘ። ስለዚህ ወደ ወህኒ ቤት ሰው ልኮ የዮሐንስን ራስ በወህኒ ቤት አስቈረጠ። የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን አምጥተው ለልጅቱ ሰጡአት፤ እርስዋም ለእናትዋ ወስዳ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት፤ ሄደውም ይህን ነገር ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስ የዮሐንስን መሞት በሰማ ጊዜ በጀልባ ተሳፈረና ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ብቻውን ለመሆን ሄደ። ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ከየከተማው እየወጡ በእግር ተከተሉት። ኢየሱስ ከጀልባው በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብን አይቶ ራራላቸው፤ በሽተኞቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቶአል፤ ስለዚህ ሕዝቡ በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች ሄደው ምግባቸውን እንዲገዙ አሰናብታቸው” አሉት። ኢየሱስ ግን፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ እነርሱ እንዲሁ ሊሄዱ አይገባም!” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “እኛ እዚህ ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው” አሉት። ኢየሱስም “እነርሱኑ ወደ እኔ አምጡልኝ!” አላቸው። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ በመስኩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አንሥቶ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ እንጀራውንም ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ዐደሉ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውን ፍርፋሪ፥ ደቀ መዛሙርቱ በዐሥራ ሁለት መሶብ ሞልተው አነሡ። የበሉትም ሰዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አምስት ሺህ ያኽል ወንዶች ነበሩ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች