ኢየሱስ ይህን ሁሉ ነገር በምሳሌ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ያለ ምሳሌም ምንም ነገር አልተናገራቸውም። ይህም የሆነበት ምክንያት በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው እንዲፈጸም ነው፦ “ንግግሬን በምሳሌ እገልጣለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውን እናገራለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን አሰናብቶ ወደ ቤት ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፥ “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም አስረዳን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻው ይህ ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ የሰይጣን ልጆች ናቸው። እንክርዳዱን የዘራው ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ነው፤ ዐጫጆቹ መላእክት ናቸው። ልክ እንክርዳዱ ተነቅሎና በየነዶው ታስሮ እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም የኃጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ከእርሱ መንግሥት ሰብስበው ያወጣሉ፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ጻድቃን ግን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻ ውስጥ የተሸሸገውን ሀብት ትመስላለች። አንድ ሰው ይህን ሀብት ባገኘው ጊዜ መልሶ ደበቀው፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ ሄደና ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛ።” እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ደግሞ መንግሥተ ሰማይ ጥሩ ዕንቊ ለመግዛት የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ ነጋዴውም እጅግ ክቡር የሆነ ዕንቊ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያንን ዕንቊ ገዛ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር የተጣለች መረብን ትመስላለች፤ እርስዋ በየዐይነቱ ዓሣ የምትሰበስብ ናት፤ በሞላች ጊዜ ዓሣ አጥማጆቹ ወደ ባሕሩ ዳር ጐትተው ያወጡአታል፤ ተቀምጠውም መልካም መልካሙን መርጠው በዕቃ ያስቀምጣሉ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ወዲያ ይጥላሉ። በዓለም መጨረሻም እንዲህ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል። ክፉዎችን ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ደግሞም ኢየሱስ፦ “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉ። እርሱም “እንግዲያውስ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሕግ መምህር፦ ከዕቃ ግምጃ ቤቱ አዲስ የሆነውንና አሮጌ የሆነውን ዕቃ የሚያመጣ የንብረት ባለቤትን ይመስላል” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ተናግሮ ካበቃ በኋላ፥ ከዚያ ስፍራ ሄደ። ወደ አገሩ ወደ ናዝሬት ከተማ መጥቶ በምኲራቦቻቸው ሕዝብን ያስተምር ነበር፤ የሰሙትም ሁሉ በመደነቅ እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና ይህን ድንቅ ሥራ ከወዴት አመጣው? ይህ የአናጢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም የምትባል አይደለችምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፥ ዮሴፍ፥ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ ከእኛ ጋር አይደሉምን? ታዲያ፥ ይህ ሰው ይህን ሁሉ ጥበብ ከየት አገኘው?” በዚህም ምክንያት ተሰናክለውበት ሳይቀበሉት ቀሩ። ኢየሱስ ግን፦ “ነቢይ የማይከበረው በሀገሩና በገዛ ቤቱ ብቻ ነው” አላቸው። ባለማመናቸውም ኢየሱስ በዚያ ብዙ ተአምር አላደረገም።
የማቴዎስ ወንጌል 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 13:34-58
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች