ማቴዎስ 13:34-58
ማቴዎስ 13:34-58 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም “በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ፤” የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም። በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን፤” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው “መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፤ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፤ አጫጆችም መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፤ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፤ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ። “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት። “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዐይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፤ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ፤ ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኀጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፤ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ኢየሱስም “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው፤ “አዎን” አሉት። እርሱም “ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል፤” አላቸው። ኢየሱስም እነዚህም ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ “ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው? ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ፥ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው?” ተሰናከሉበትም። ኢየሱስ ግን “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።
ማቴዎስ 13:34-58 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። በዚህም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ።” ከዚያም ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፣ “በዕርሻው ውስጥ ስላለው እንክርዳድ የተናገርኸውን ምሳሌ ትርጕም ንገረን” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ጥሩውን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ ዕርሻውም ይህ ዓለም ነው፤ ጥሩው ዘር የእግዚአብሔርን መንግሥት ልጆች ያመለክታል፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፤ ዘርቶት የሄደው ጠላትም ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ሲሆን፣ ዐጫጆቹም መላእክት ናቸው። “እንክርዳዱ ተነቅሎ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም ለኀጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ የሚያደርጉትን ሁሉ ለቅመው ከመንግሥቱ ያወጣሉ። ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል። በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሓይ ያበራሉ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ። “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፤ አንድ ሰው ባገኛት ጊዜ መልሶ ሸሸጋት፤ ከመደሰቱም የተነሣ፣ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያን የዕርሻ ቦታ ገዛ። “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ውብ ዕንቍ የሚፈልግ ነጋዴ ትመስላለች፤ እጅግ ውድ የሆነ ዕንቍ ባገኘም ጊዜ፣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ገዛው። “ደግሞም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር ተጥሎ የዓሣ ዐይነቶችን የያዘ መረብ ትመስላለች፤ ዓሣ አጥማጆቹ መረቡ ሲሞላላቸው ጐትተው ወደ ባሕሩ ዳር አወጡት፤ ከዚያም ተቀምጠው ጥሩ ጥሩውን እየለዩ በቅርጫት ውስጥ ጨመሩ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ጣሉት። በዓለም መጨረሻም ልክ እንደዚሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኀጢአተኞችን ከጻድቃን በመለየት፣ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል።” ኢየሱስ፣ “ይህ ሁሉ ገብቷችኋል?” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን” አሉት። እርሱም፣ “ስለዚህም የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር የተረዳ ማንኛውም የኦሪት ሕግ መምህር፣ ከከበረ ሀብቱ ክምችት አዲሱንም አሮጌውንም የሚያወጣ ባለንብረት ይመስላል” አላቸው። ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች እንደ ጨረሰ፣ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ሄደ፤ ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ በምኵራባቸውም ሕዝቡን ያስተምር ጀመር። እነርሱም በመገረም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና እነዚህን ታምራት የማድረግ ኀይል ከየት አገኘ? ይህ የዐናጺው ልጅ አይደለምን? የእናቱስ ስም ማርያም አይደለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? እኅቶቹስ ከእኛው ጋራ አይደሉምን? ታዲያ ይህ ሰው ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት። ኢየሱስ ግን፣ “ነቢይ የማይከበረው በራሱ አገርና በራሱ ቤት ብቻ ነው” አላቸው። ባለማመናቸውም ምክንያት ብዙ ታምራትን በዚያ አላደረገም።
ማቴዎስ 13:34-58 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም፦ በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም። በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፦ የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ደግሞ መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፥ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ። ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት። ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፥ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ኢየሱስም፦ ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን? አላቸው፤ አዎን አሉት። እርሱም፦ ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል አላቸው። ኢየሱስም እነዚህም ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ፦ ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው? ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው? ተሰናከሉበትም። ኢየሱስ ግን፦ ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።
ማቴዎስ 13:34-58 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ይህን ሁሉ ነገር በምሳሌ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ያለ ምሳሌም ምንም ነገር አልተናገራቸውም። ይህም የሆነበት ምክንያት በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው እንዲፈጸም ነው፦ “ንግግሬን በምሳሌ እገልጣለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውን እናገራለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን አሰናብቶ ወደ ቤት ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፥ “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም አስረዳን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻው ይህ ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ የሰይጣን ልጆች ናቸው። እንክርዳዱን የዘራው ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ነው፤ ዐጫጆቹ መላእክት ናቸው። ልክ እንክርዳዱ ተነቅሎና በየነዶው ታስሮ እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም የኃጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ከእርሱ መንግሥት ሰብስበው ያወጣሉ፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ጻድቃን ግን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻ ውስጥ የተሸሸገውን ሀብት ትመስላለች። አንድ ሰው ይህን ሀብት ባገኘው ጊዜ መልሶ ደበቀው፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ ሄደና ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛ።” እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ደግሞ መንግሥተ ሰማይ ጥሩ ዕንቊ ለመግዛት የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ ነጋዴውም እጅግ ክቡር የሆነ ዕንቊ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያንን ዕንቊ ገዛ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር የተጣለች መረብን ትመስላለች፤ እርስዋ በየዐይነቱ ዓሣ የምትሰበስብ ናት፤ በሞላች ጊዜ ዓሣ አጥማጆቹ ወደ ባሕሩ ዳር ጐትተው ያወጡአታል፤ ተቀምጠውም መልካም መልካሙን መርጠው በዕቃ ያስቀምጣሉ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ወዲያ ይጥላሉ። በዓለም መጨረሻም እንዲህ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል። ክፉዎችን ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ደግሞም ኢየሱስ፦ “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉ። እርሱም “እንግዲያውስ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሕግ መምህር፦ ከዕቃ ግምጃ ቤቱ አዲስ የሆነውንና አሮጌ የሆነውን ዕቃ የሚያመጣ የንብረት ባለቤትን ይመስላል” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ተናግሮ ካበቃ በኋላ፥ ከዚያ ስፍራ ሄደ። ወደ አገሩ ወደ ናዝሬት ከተማ መጥቶ በምኲራቦቻቸው ሕዝብን ያስተምር ነበር፤ የሰሙትም ሁሉ በመደነቅ እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና ይህን ድንቅ ሥራ ከወዴት አመጣው? ይህ የአናጢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም የምትባል አይደለችምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፥ ዮሴፍ፥ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ ከእኛ ጋር አይደሉምን? ታዲያ፥ ይህ ሰው ይህን ሁሉ ጥበብ ከየት አገኘው?” በዚህም ምክንያት ተሰናክለውበት ሳይቀበሉት ቀሩ። ኢየሱስ ግን፦ “ነቢይ የማይከበረው በሀገሩና በገዛ ቤቱ ብቻ ነው” አላቸው። ባለማመናቸውም ኢየሱስ በዚያ ብዙ ተአምር አላደረገም።
ማቴዎስ 13:34-58 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ነገራቸው፤ ያለ ምሳሌም ምንም አልነገራቸውም። ይህም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ፤” በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም ንገረን፤” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የመንግሥቱ ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ ደግሞ የክፉው ልጆች ናቸው፤ የዘራው ጠላት ደግሞ ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፤ አጫጆቹ መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ ከመንግሥቱም እንቅፋቶችን ሁሉና ዓመፃን ይሰበስባሉ፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው በእርሻ ውስጥ አግኝቶ መልሶ የሸሸገው የተሰወረ መዝገብ ትመስላለች፤ ከደስታውም ብዛት ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛው። “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ክቡር ዕንቁ የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋ እጅግ ውድ የሆነ አንዲት ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት። “ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለችና ከሁሉም ዓይነት ዓሣ የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላች ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፤ ተቀምጠውም መልካሞቹን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አስቀመጡ፤ ክፉውን ግን ጣሉት። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ክፉዎችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው፤ “አዎን” አሉት። እርሱም “ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀመዝሙር የሆነ ጸሐፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል፤” አላቸው። ኢየሱስም እነዚህን ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ በምኵራባቸው ያስተምራቸው ነበር፥ ተገርመውም እንዲህም አሉ “ይህን ጥበብና ኃይል ከየት አገኘው? ይህ የጠራቢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፥ ዮሴፍ፥ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ ከእኛ ጋር ያሉ አይደሉምን? ታዲያ ይህን ሁሉ ከየት አገኘው?” ተሰናከሉበትም። ኢየሱስ ግን “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በስተቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። ባለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።