የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 12:22-50

የማቴዎስ ወንጌል 12:22-50 አማ05

ከዚህ በኋላ ሰዎች አንድ ጋኔን ያደረበትን ዕውርና ድዳ ሰው ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም ፈወሰው፤ ሰውየውም መናገርና ማየት ቻለ። ሕዝቡም ሁሉ ተገርመው፥ “ይህ የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። ፈሪሳውያን ግን ይህን በሰሙ ጊዜ “እርሱ ‘ብዔልዜቡል’ በተባለው በአጋንንት አለቃ አማካይነት ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም” አሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ መንግሥት ተከፋፍሎ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ከሆነ፥ ያ መንግሥት ይወድቃል። እንዲሁም አንድ ከተማ ወይም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ጸንቶ መኖር አይችልም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ እርስ በርሱ ተለያየ ማለት ነው፤ ታዲያ፥ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊኖር ይችላል! ደግሞ እኔ አጋንንትን የማስወጣቸው በብዔልዜቡል ከሆነ፥ ልጆቻችሁስ በምን ያስወጡአቸዋል? ስለዚህ ልጆቻችሁ በእናንተ ላይ ይፈርዱባችኋል። እኔ አጋንንትን የማስወጣ በእግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ ግን እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት በእናንተ ላይ መጥታለች ማለት ነው። ደግሞስ አንድ ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሳያስር ወደ ኀይለኛው ቤት ገብቶ ንብረቱን መዝረፍ እንዴት ይችላል? ኀይለኛውን ካሰረው በኋላ ግን በእርግጥ ንብረቱን ሊዘርፍ ይችላል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ተቃዋሚዬ ነው፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል። ስለዚህ ሰው የሚያደርገው ማናቸውም ኃጢአት ወይም የስድብ ቃል ሁሉ ይቅር ይባልለታል እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሰው ግን በደሉ ይቅር አይባልለትም። በሰው ልጅ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ በደሉ ይቅር ይባልለታል። በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ ግን በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም በደሉ ይቅር አይባልለትም። “ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ ፍሬውም መልካም ይሆናል፤ ዛፉ መጥፎ ከሆነ ግን ፍሬውም መጥፎ ይሆናል። እናንተ የእባብ ልጆች! ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ነገር መናገር እንዴት ትችላላችሁ? ሰው በአፉ የሚናገረው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው። “መልካም ሰው ከመልካም መዝገቡ፥ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገቡ ክፉ ነገርን ያወጣል። በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰዎች በግዴለሽነት በሚናገሩት በያንዳንዱ ቃል በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል። ከቃልህ የተነሣ ይፈረድልሃል፤ ከቃልህም የተነሣ ይፈረድብሃል።” በዚያን ጊዜ አንዳንድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ! አንተ ተአምር ስታደርግ ማየት እንፈልጋለን!” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ክፉና የማያምን ትውልድ ተአምር ለማየት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ተአምር በቀር ሌላ ተአምር አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንዳሳለፈ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በመቃብር ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ያሳልፋል። የነነዌ ከተማ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ዘመን ትውልድ ጋር ተነሥተው በእርሱ ላይ ይፈርዱበታል፤ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት በሰሙ ጊዜ በኃጢአታቸው ተጸጽተው ንስሓ ገብተዋልና። አሁን ግን ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። የደቡብ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ ስለ መጣች በፍርድ ቀን ከዚህ ዘመን ትውልድ ጋር ተነሥታ በእርሱ ላይ ትፈርድበታለች፤ አሁን ግን ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ርኩስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ የሚያርፍበት ቦታ በመፈለግ ውሃ በሌለበት በደረቅ ቦታ ይዞራል። ነገር ግን አያገኝም፤ ስለዚህ ‘ወደ ወጣሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል። ተመልሶም ሲመጣ፥ ቤቱ ባዶ ሆኖ፥ ጸድቶ፥ ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚህ በኋላ፥ ርኩሱ መንፈስ ይሄድና ከእርሱ ይብስ የከፉትን ሌሎች ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል። እነርሱም ቀድሞ የጋኔኑ ቤት ወደ ነበረው ሰው ልብ ገብተው አብረው በዚያ ይኖራሉ። ስለዚህ የዚያ ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከመጀመሪያው ይልቅ የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድ ላይ የሚሆነው ይህንኑ የመሰለ ነገር ነው።” ኢየሱስ ለሕዝቡ ገና ሲናገር ሳለ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። [ እዚያ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ኢየሱስን፥ “እነሆ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጪ ቆመዋል” አለው።] ኢየሱስ ግን “እናቴ ማናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰ። ከዚህ በኋላ እጁን ዘርግቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፦ “እናቴና ወንድሞቼ እነሆ፥ እነዚህ ናቸው፤ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም ሁሉ፥ ወንድሜም፥ እኅቴም፥ እናቴም እርሱ ነው።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች

Free Reading Plans and Devotionals related to የማቴዎስ ወንጌል 12:22-50