የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 9:37-62

የሉቃስ ወንጌል 9:37-62 አማ05

በማግስቱ ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ከተራራው በወረዱ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስን ተገናኙት። ከሕዝቡም መካከል አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጮኸ! “መምህር ሆይ፥ ይህ ለኔ አንድ ልጅ ነውና እንድታድንልኝ እለምንሃለሁ፤ እነሆ! ርኩስ መንፈስ በድንገት ይዞ ያስጮኸዋል፤ በመሬት ላይ ጥሎ ዐረፋ እያስደፈቀ ያንፈራግጠዋል፤ ሰውነቱንም እያቈሰለ በአሳር ይለቀዋል። ርኩሱን መንፈስ እንዲያስወጡለት ደቀ መዛሙርትህን ጠይቄአቸው ነበር፤ ነገር ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እናንተ እምነት የሌላችሁ ጠማማ ትውልድ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጅህን ወዲህ አምጣው።” ልጁም ወደ ኢየሱስ በቀረበ ጊዜ ጋኔኑ በመሬት ላይ ጥሎ አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው፤ ልጁንም ፈውሶ ለአባቱ ሰጠው። ሕዝቡም ሁሉ የእግዚአብሔርን ታላቅ ኀይል በማየታቸው ተገረሙ፤ ሁሉም ኢየሱስ ባደረገው ነገር በመደነቅ ላይ ሳሉ እርሱ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ይህን የምነግራችሁን ቃል ልብ ብላችሁ አስተውሉ! እነሆ፥ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል።” እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉም፤ የንግግሩም ምሥጢር ተሰውሮባቸው ነበር፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። ደቀ መዛሙርቱ “ከእኛ ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” በማለት ክርክር አንሥተው ነበር። ኢየሱስ ግን የልባቸውን ሐሳብ ዐውቆ አንድ ሕፃን ልጅ አመጣና በአጠገቡ አቆመው፤ እርሱም “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ የላከኝን ይቀበላል። ከእናንተ መካከል ከሁላችሁም የሚያንስ እርሱ ከሁሉ የሚበልጥ ይሆናል፤” አላቸው። ከዚህም በኋላ ዮሐንስ ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየነው፤ ነገር ግን ከእኛ ጋር ስላልሆነ ከለከልነው፤” አለ። ኢየሱስም “የማይቃወማችሁ ሁሉ ከእናንተ ጋር ስለ ሆነ ተዉ፤ አትከልክሉት!” አለ። ኢየሱስ የሚያርግበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ። ከእርሱ በፊት ቀድመው የሚሄዱትንም መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ሁሉን ነገር ለማዘጋጀት በሰማርያ ወደምትገኘው ወደ አንዲት መንደር ሄዱ። ነገር ግን እርሱ በዚያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄድ መሆኑን ዐውቀው ስለ ነበር የዚያች መንደር ሰዎች ሊቀበሉት አልፈለጉም። ደቀ መዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ባዩ ጊዜ፥ “ጌታ ሆይ! ከሰማይ እሳት ወርዶ እነዚህን ሰዎች ያቃጥላቸው ዘንድ እንድናዝዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ ገሠጻቸው። [እናንተ ከምን ዐይነት መንፈስ እንደ ሆናችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የመጣው የሰውን ሕይወት ለማዳን ነው እንጂ፥ ለማጥፋት አይደለም።] ከዚያም ተነሥተው ወደ ሌላ መንደር ሄዱ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ጒዞ ቀጥለው በመንገድ ላይ ሳሉ አንድ ሰው ኢየሱስን “እኔ ወደምትሄድበት ሁሉ ልከተልህ እፈልጋለሁ፤” አለው። ኢየሱስም “ቀበሮዎች ጒድጓድ አላቸው፤ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ አስጠግቶ የሚያሳርፍበት ስፍራ የለውም፤” ሲል መለሰለት። ሌላውንም ሰው “ተከተለኝ!” አለው። ሰውየው ግን “ጌታ ሆይ! መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ፤” አለው። ኢየሱስም “ሙታንን ተዋቸው፤ ሙታኖቻቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ግን ሂድና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተምር!” ሲል መለሰለት። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “ጌታ ሆይ፥ እኔ ልከተልህ እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን መጀመሪያ ሄጄ ቤተሰቤን እንድሰናበት ፍቀድልኝ፤” አለው። ኢየሱስም “ለማረስ በእጁ ዕርፍ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም፤” ሲል መለሰለት።