ኢየሱስ ከጀልባ ወደ ምድር በወረደ ጊዜ አጋንንት ያደሩበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ ተገናኘው፤ ይህ ሰው ልብሱን ከጣለ ብዙ ጊዜው ነበር፤ የሚኖረውም በመቃብር ቦታ እንጂ በቤት ውስጥ አልነበረም። ኢየሱስን ባየ ጊዜ ጮኸ፤ በኢየሱስ ፊትም ወደቀና ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከእኔ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? እባክህ አታሠቃየኝ፤” አለው። ይህንንም ያለበት ምክንያት ኢየሱስ ርኩሱን መንፈስ ከሰውየው እንዲወጣ አዞት ስለ ነበር ነው። ከዚህ በፊት ርኩሱ መንፈስ በሰውየው ላይ ብዙ ጊዜ ይነሣበት ነበር፤ በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ይጠበቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሰንሰለቱን ይበጥስ፥ እግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ጋኔኑም እየነዳ ወደ በረሓ ይወስደው ነበር። ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም ብዙ አጋንንት ሰፍረውበት ስለ ነበር “ስሜ ሌጌዎን ነው” ሲል መለሰለት። ወዲያውም አጋንንቱም “እባክህ ወደ ጥልቁ ገደል አትስደደን” ሲሉ ለመኑት። በዚያም ስፍራ በኮረብታ ጥግ የብዙ ዐሣማዎች መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ አጋንንቱ “ወደ ዐሣማዎቹ እንድንገባ ፍቀድልን” ሲሉ ኢየሱስን ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። ስለዚህ አጋንንቱ ከሰውየው ወጥተው በዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ዐሣማዎቹ ከገደሉ ላይ እየተንደረደሩ ወረዱ፤ ወደ ባሕር ገብተውም ሰጠሙ። የዐሣማዎቹም እረኞች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ ሸሽተው ሄዱ፤ በየከተማውና በየገጠሩም ወሬውን አዳረሱ። ሰዎቹም የሆነውን ነገር ለማየት ከየቤታቸው ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ አጋንንት የወጡለትንም ሰው ልቡናው ተመልሶለትና ልብሱንም ለብሶ በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጦ ባዩት ጊዜ ፈሩ፤ የዐይን ምስክር የነበሩ ሰዎችም አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው። ከዚህ በኋላ የጌርጌሴኖን አካባቢ ሰዎች ሁሉ ኢየሱስ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት። ይህንንም ያሉበት ምክንያት በጣም ፈርተው ስለ ነበረ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በጀልባ ተሳፈረና ወደ መጣበት ስፍራ ተመልሶ ሄደ። አጋንንት የወጡለትም ሰው ኢየሱስን “እባክህ ልከተልህ፤” ብሎ ለመነው። ኢየሱስ ግን እንዲህ ብሎ አሰናበተው። “ወደ ቤትህ ሂድና እግዚአብሔር ያደረገልህን ሁሉ ተናገር!”፤ ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ትልቅ ነገር በከተማው ሁሉ እየተናገረ ሄደ። ሕዝቡ ይጠባበቀው ስለ ነበር ኢየሱስ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ሁሉም በደስታ ተቀበሉት። በዚያን ጊዜ አንድ የምኲራብ አለቃ የሆነ፥ ኢያኢሮስ የተባለ ሰው መጣ፤ በኢየሱስ እግር ሥር ወድቆ፥ “እባክህ ወደ ቤቴ ናልኝ፤” ብሎ ለመነው። ይህንንም ያለው ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆናት አንድያ ልጁ ታማ በሞት አፋፍ ላይ ስለ ነበረች ነው። ኢየሱስም ከእርሱ ጋር አብሮ ሲሄድ ሳለ ተከትለውት የነበሩ ብዙ ሰዎች በመጨናነቅ ይጋፉ ነበር። ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም እየመታት የምትሠቃይ አንዲት ሴት ነበረች፤ እርስዋም ያላትን ገንዘብ ሁሉ ለሐኪሞች በመክፈል ጨርሳ ማንም ሊያድናት አልቻለም። እርስዋ ወደ ኢየሱስ መጥታ ከበስተኋላው ቀረበችና የልብሱን ጫፍ ነካች፤ ወዲያውኑ ደምዋ መፍሰሱን አቆመ። ኢየሱስም “ማን ነው የነካኝ?” ሲል ጠየቀ። ሁሉም “እኛ አልነካንህም፤” አሉ፤ ጴጥሮስም “መምህር ሆይ፥ ሕዝቡ እየተጋፋ ሲከተልህ እያየህ ማን ነው የነካኝ ትላለህን?” አለው። ኢየሱስ ግን “ኀይል ከእኔ መውጣቱን ዐውቄአለሁና በእርግጥ አንድ ሰው ነክቶኛል፤” አለ። ሴትዮዋም እንዳልተሰወረች ባወቀች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች ወደ ኢየሱስ መጥታ በእግሩ ሥር ወደቀች፤ ከዚያም በኋላ ለምን እንደ ነካችውና እንዴት ወዲያውኑ እንደ ተፈወሰችም በሕዝቡ ሁሉ ፊት ገለጠች። ኢየሱስም “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ!” አላት። ኢየሱስ ገና ይህንን በመናገር ላይ ሳለ አንድ ሰው ከምኲራብ አለቃው ከኢያኢሮስ ቤት መጥቶ “ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህሩን በከንቱ አታድክመው!” አለው። ኢየሱስ ግን ይህን ሰምቶ ኢያኢሮስን፥ “አይዞህ አትፍራ፤ እመን ብቻ፤ ልጅህ ትድናለች፤” አለው። ኢየሱስ ወደ ኢያኢሮስ ቤት በደረሰ ጊዜ ከጴጥሮስ፥ ከዮሐንስ፥ ከያዕቆብ፥ ከልጅትዋ አባትና እናት በቀር ሌላ ማንም ከእርሱ ጋር ወደ ውስጥ እንዲገባ አልፈቀደም። በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ስለ ልጅትዋ ያለቅሱ! ዋይ ዋይም ይሉ ነበር። ኢየሱስ ግን “አታልቅሱ፤ ልጅትዋ አንቀላፍታለች እንጂ አልሞተችም፤” አላቸው። እነርሱ ግን ልጅትዋ መሞትዋን ስላወቁ ሁሉም በማፌዝ ሳቁበት። ኢየሱስ የልጅትዋን እጅ ይዞ፦ “አንቺ ልጅ፥ ተነሽ!” አላት። እርስዋም ነፍስዋ ስለ ተመለሰችላት ወዲያውኑ ብድግ አለች፤ ኢየሱስም “የምትበላውን ስጡአት!” ሲል አዘዘ። የልጅትዋም ወላጆች ተገረሙ፤ እርሱ ግን የሆነውን ነገር ለማንም አትናገሩ ሲል አዘዛቸው።
የሉቃስ ወንጌል 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 8:27-56
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች