የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 8

8
ኢየሱስን ይከተሉ የነበሩ ሴቶች
1ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየከተማውና በየመንደሩ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከና የምሥራች እያበሠረ ያልፍ ነበር፤ ዐሥራ ሁለቱም አብረውት ነበሩ። 2እንዲሁም ከርኩሳን መናፍስት የተላቀቁና ከበሽታ የተፈወሱ ሴቶች ኢየሱስን ይከተሉት ነበር፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፥ 3የሄሮድስ ቤት አዛዥ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናና ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህ ሴቶች ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን በገንዘባቸው ያገለግሉ ነበር። #ማቴ. 27፥55-56፤ ማር. 15፥40-44፤ ሉቃ. 23፥49።
የዘሪው ምሳሌ
(ማቴ. 13፥1-9ማር. 4፥1-9)
4ብዙ ሕዝብ ከየከተማው ወደ እርሱ መጥተው በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤
5“አንድ ገበሬ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ተረገጠ፤ ወፎችም በሉት። 6ሌላውም ዘር በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መሬቱ እርጥበት ስላልነበረው ቡቃያው ደረቀ። 7ሌላውም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹ አብሮ አደገና አንቆ አስቀረው። 8ሌላው ዘር ግን በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለ፤ ቡቃያውም አድጎ እያንዳንዱ መቶ እጥፍ አፈራ።”
ቀጥሎም ኢየሱስ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” አለ።
ኢየሱስ በምሳሌ የተናገረበት ምክንያት
(ማቴ. 13፥10-17ማር. 4፥10-12)
9ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “የዚህ ምሳሌ ትርጒም ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። 10ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ሌሎች ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ እነርሱ እያዩ ልብ እንዳያደርጉ፥ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።”
የዘሪው ምሳሌ ትርጒም
(ማቴ. 13፥18-23ማር. 4፥13-20) #ኢሳ. 6፥9-10
11የምሳሌው ትርጒም ይህ ነው፦ “ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ 12በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። 13በጭንጫማ መሬት ላይ የወደቀውም ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ሰምተው በደስታ የሚቀበሉትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ የሚያምኑት ለጊዜው ነው፤ ሥር ስለሌላቸውም በፈተና ጊዜ ወዲያውኑ ይክዳሉ። 14በእሾኽም ቊጥቋጦ መካከል የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ሐሳብና ሀብት፥ የምድራዊ ኑሮ ምቾትም አንቆ ያለ ፍሬ ያስቀራቸዋል። 15በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ግን በመልካምና በቅን ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁትን ነው፤ እነርሱ በቃሉ ጸንተው ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”
መብራት የሚበራው ብርሃን እንዲሰጥ መሆኑ
(ማር. 4፥21-25)
16ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መብራት አብርቶ እንቅብ የሚደፋበት ወይም በአልጋ ሥር የሚያኖረው ማንም የለም፤ ይልቅስ ወደ ቤት የሚገቡ ሁሉ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል። #ማቴ. 5፥15፤ ሉቃ. 11፥33።
17“እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረ ሳይታወቅ የሚቀር የለም። #ማቴ. 10፥26፤ ሉቃ. 12፥2።
18“ስለዚህ ቃሉን እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ሰው ተጨምሮ ይሰጠዋል፤ የሌለው ግን አለኝ ብሎ የሚያስበው እንኳ ይወሰድበታል።” #ማቴ. 25፥29፤ ሉቃ. 19፥26።
የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ
(ማቴ. 12፥46-50ማር. 3፥31-35)
19የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ ወደ እርሱ መጡ፤ ነገር ግን ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሊያገኙት አልቻሉም። 20ስለዚህ “እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ በውጪ ቆመው ሊያዩህ ይፈልጋሉ፤” ብለው ሰዎች ነገሩት።
21ኢየሱስም “የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚፈጽሙት ሁሉ እነርሱ እናቴና ወንድሞቼ ናቸው፤” አለ።
ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ ማድረጉ
(ማቴ. 8፥23-27ማር. 4፥35-41)
22አንድ ቀን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ተሳፈረና “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር፤” አላቸው፤ እነርሱም ለመሄድ ተነሡ። 23በባሕሩ ላይ እየቀዘፉ ሲሄዱ ሳሉ ኢየሱስ አንቀላፋ፤ በዚያን ጊዜ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ በባሕሩ ላይ ተነሣ፤ ውሃውም በጀልባው ውስጥ መሙላት ስለ ጀመረ አደጋው አስግቶአቸው ነበር። 24ደቀ መዛሙርቱ “መምህር ሆይ! መምህር ሆይ! ልናልቅ ነው!” ሲሉ ኢየሱስን ቀሰቀሱት።
እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የሚያናውጠውን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ነፋሱና የሚያናውጠው ማዕበል ወዲያውኑ ቆሙ፤ ታላቅ ጸጥታም ሆነ። 25ከዚያም በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፥ “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው። እነርሱ ግን እጅግ ተደንቀውና ፈርተው እርስ በርሳቸው፥ “ነፋስንና ማዕበልን ያዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤ ለመሆኑ ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።
ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን ሰው መፈወሱ
(ማቴ. 8፥28-34ማር. 5፥1-20)
26ባሕሩንም ተሻግረው በገሊላ ማዶ ወደምትገኘው ወደ ጌርጌሴኖን አገር ደረሱ፤ 27ኢየሱስ ከጀልባ ወደ ምድር በወረደ ጊዜ አጋንንት ያደሩበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ ተገናኘው፤ ይህ ሰው ልብሱን ከጣለ ብዙ ጊዜው ነበር፤ የሚኖረውም በመቃብር ቦታ እንጂ በቤት ውስጥ አልነበረም። 28ኢየሱስን ባየ ጊዜ ጮኸ፤ በኢየሱስ ፊትም ወደቀና ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከእኔ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? እባክህ አታሠቃየኝ፤” አለው። 29ይህንንም ያለበት ምክንያት ኢየሱስ ርኩሱን መንፈስ ከሰውየው እንዲወጣ አዞት ስለ ነበር ነው። ከዚህ በፊት ርኩሱ መንፈስ በሰውየው ላይ ብዙ ጊዜ ይነሣበት ነበር፤ በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ይጠበቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሰንሰለቱን ይበጥስ፥ እግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ጋኔኑም እየነዳ ወደ በረሓ ይወስደው ነበር።
30ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም ብዙ አጋንንት ሰፍረውበት ስለ ነበር “ስሜ ሌጌዎን ነው” ሲል መለሰለት። #8፥30 ሌጌዎን፦ ሌጌዎን ማለት ሠራዊት ወይም ጭፍራ ማለት ነው። 31ወዲያውም አጋንንቱም “እባክህ ወደ ጥልቁ ገደል አትስደደን” ሲሉ ለመኑት።
32በዚያም ስፍራ በኮረብታ ጥግ የብዙ ዐሣማዎች መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ አጋንንቱ “ወደ ዐሣማዎቹ እንድንገባ ፍቀድልን” ሲሉ ኢየሱስን ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። 33ስለዚህ አጋንንቱ ከሰውየው ወጥተው በዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ዐሣማዎቹ ከገደሉ ላይ እየተንደረደሩ ወረዱ፤ ወደ ባሕር ገብተውም ሰጠሙ።
34የዐሣማዎቹም እረኞች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ ሸሽተው ሄዱ፤ በየከተማውና በየገጠሩም ወሬውን አዳረሱ። 35ሰዎቹም የሆነውን ነገር ለማየት ከየቤታቸው ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ፤ አጋንንት የወጡለትንም ሰው ልቡናው ተመልሶለትና ልብሱንም ለብሶ በኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጦ ባዩት ጊዜ ፈሩ፤ 36የዐይን ምስክር የነበሩ ሰዎችም አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው። 37ከዚህ በኋላ የጌርጌሴኖን አካባቢ ሰዎች ሁሉ ኢየሱስ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት። ይህንንም ያሉበት ምክንያት በጣም ፈርተው ስለ ነበረ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በጀልባ ተሳፈረና ወደ መጣበት ስፍራ ተመልሶ ሄደ። 38አጋንንት የወጡለትም ሰው ኢየሱስን “እባክህ ልከተልህ፤” ብሎ ለመነው። ኢየሱስ ግን እንዲህ ብሎ አሰናበተው።
39“ወደ ቤትህ ሂድና እግዚአብሔር ያደረገልህን ሁሉ ተናገር!”፤ ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ትልቅ ነገር በከተማው ሁሉ እየተናገረ ሄደ።
የኢያኢሮስ ልጅና የኢየሱስን ልብስ የነካች ሴት
(ማቴ. 9፥18-26ማር. 5፥21-43)
40ሕዝቡ ይጠባበቀው ስለ ነበር ኢየሱስ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ሁሉም በደስታ ተቀበሉት። 41በዚያን ጊዜ አንድ የምኲራብ አለቃ የሆነ፥ ኢያኢሮስ የተባለ ሰው መጣ፤ በኢየሱስ እግር ሥር ወድቆ፥ “እባክህ ወደ ቤቴ ናልኝ፤” ብሎ ለመነው። 42ይህንንም ያለው ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆናት አንድያ ልጁ ታማ በሞት አፋፍ ላይ ስለ ነበረች ነው።
ኢየሱስም ከእርሱ ጋር አብሮ ሲሄድ ሳለ ተከትለውት የነበሩ ብዙ ሰዎች በመጨናነቅ ይጋፉ ነበር። 43ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም እየመታት የምትሠቃይ አንዲት ሴት ነበረች፤ እርስዋም ያላትን ገንዘብ ሁሉ ለሐኪሞች በመክፈል ጨርሳ ማንም ሊያድናት አልቻለም። 44እርስዋ ወደ ኢየሱስ መጥታ ከበስተኋላው ቀረበችና የልብሱን ጫፍ ነካች፤ ወዲያውኑ ደምዋ መፍሰሱን አቆመ። 45ኢየሱስም “ማን ነው የነካኝ?” ሲል ጠየቀ።
ሁሉም “እኛ አልነካንህም፤” አሉ፤ ጴጥሮስም “መምህር ሆይ፥ ሕዝቡ እየተጋፋ ሲከተልህ እያየህ ማን ነው የነካኝ ትላለህን?” አለው።
46ኢየሱስ ግን “ኀይል ከእኔ መውጣቱን ዐውቄአለሁና በእርግጥ አንድ ሰው ነክቶኛል፤” አለ። 47ሴትዮዋም እንዳልተሰወረች ባወቀች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች ወደ ኢየሱስ መጥታ በእግሩ ሥር ወደቀች፤ ከዚያም በኋላ ለምን እንደ ነካችውና እንዴት ወዲያውኑ እንደ ተፈወሰችም በሕዝቡ ሁሉ ፊት ገለጠች። 48ኢየሱስም “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ!” አላት።
49ኢየሱስ ገና ይህንን በመናገር ላይ ሳለ አንድ ሰው ከምኲራብ አለቃው ከኢያኢሮስ ቤት መጥቶ “ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህሩን በከንቱ አታድክመው!” አለው።
50ኢየሱስ ግን ይህን ሰምቶ ኢያኢሮስን፥ “አይዞህ አትፍራ፤ እመን ብቻ፤ ልጅህ ትድናለች፤” አለው።
51ኢየሱስ ወደ ኢያኢሮስ ቤት በደረሰ ጊዜ ከጴጥሮስ፥ ከዮሐንስ፥ ከያዕቆብ፥ ከልጅትዋ አባትና እናት በቀር ሌላ ማንም ከእርሱ ጋር ወደ ውስጥ እንዲገባ አልፈቀደም። 52በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ስለ ልጅትዋ ያለቅሱ! ዋይ ዋይም ይሉ ነበር። ኢየሱስ ግን “አታልቅሱ፤ ልጅትዋ አንቀላፍታለች እንጂ አልሞተችም፤” አላቸው።
53እነርሱ ግን ልጅትዋ መሞትዋን ስላወቁ ሁሉም በማፌዝ ሳቁበት። 54ኢየሱስ የልጅትዋን እጅ ይዞ፦ “አንቺ ልጅ፥ ተነሽ!” አላት። 55እርስዋም ነፍስዋ ስለ ተመለሰችላት ወዲያውኑ ብድግ አለች፤ ኢየሱስም “የምትበላውን ስጡአት!” ሲል አዘዘ። 56የልጅትዋም ወላጆች ተገረሙ፤ እርሱ ግን የሆነውን ነገር ለማንም አትናገሩ ሲል አዘዛቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ