የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 3

3
የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት
(ማቴ. 3፥1-12ማር. 1፥1-8ዮሐ. 1፥19-28)
1የሮም ንጉሠ ነገሥት ጢባርዮስ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፥ ጰንጤናዊው ጲላጦስ የይሁዳ ምድር አስተዳዳሪ ነበር፤ ሄሮድስ የገሊላ አገረ ገዢ ነበር፤ እንዲሁም ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ ገዢ፥ ሊሳኒዮስም የአቢሌኔ ገዢ ነበሩ፤ 2ሐናና ቀያፋም የካህናት አለቆች ነበሩ፤ በዚህ ጊዜ የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ በበረሓ ሳለ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። 3ስለዚህ ዮሐንስ፥ በዮርዳኖስ ወንዝ ዙሪያ ባሉት አገሮች ሁሉ እየተዘዋወረ፦ “ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ ንስሓ ገብታችሁ ተጠመቁ፤” እያለ ያስተምር ነበር። 4ይህም የሆነው፦ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ዮሐንስ አስቀድሞ እንዲህ ሲል በጻፈው መሠረት ነው፦
“እነሆ! ይህ በበረሓ እንዲህ እያለ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነው፤
‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ!
ጥርጊያውንም አቅኑ!
5ጐድጓዳው ቦታ ሁሉ ይደልደል!
ተራራና ኰረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል!
ጠማማው መንገድ ይቅና!
ሻካራውም መንገድ ይስተካከል!
6ሰውም ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ!’ ” #ኢሳ. 40፥3-5።
7ሊጠመቁ ወደ እርሱ የመጡትን ብዙ ሕዝብ ዮሐንስ እንዲህ ይላቸው ነበር፦ “እናንተ የመርዘኛ እባብ ልጆች! ከሚመጣው ከእግዚአብሔር ቊጣ እንድታመልጡ ማን አስጠነቀቃችሁ? #ማቴ. 12፥34፤ 23፥33። 8ይልቁንስ ንስሓ መግባታችሁን የሚያመለክት ሥራ ሥሩ እንጂ እኛ የአብርሃም ልጆች ነን እያላችሁ በልባችሁ አትመኩ። እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እንደሚችል እነግራችኋለሁ። #ዮሐ. 8፥33። 9አሁን መጥረቢያ በዛፎቹ ሥር ተቀምጦአል። ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።” #ማቴ. 7፥19።
10ሕዝቡም “ታዲያ፥ ምን እናድርግ?” ሲሉ ዮሐንስን ጠየቁት።
11እርሱም፦ “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለሌለው ይስጥ፤ ምግብ ያለውም ለሌለው ያካፍል፤” አላቸው።
12ቀራጮችም ሊጠመቁ ወደ እርሱ መጥተው “መምህር ሆይ! እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። #ሉቃ. 7፥29።
13እርሱም፦ “በሕግ ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትጠይቁ፤” አላቸው።
14ወታደሮችም መጥተው፥ “እኛስ ምን እናድርግ?” አሉት፤
እርሱም፦ “የሰው ገንዘብ በግፍ ነጥቃችሁ አትውሰዱ፤ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፤ የራሳችሁ ደመወዝ ይብቃችሁ፤” አላቸው።
15በዚያን ዘመን ሕዝቡ ሁሉ የመሲሕን መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ ነበር፤ ስለዚህ ዮሐንስን “ይህ ሰው ምናልባት መሲሕ ይሆንን?” እያሉ በልባቸው አሰቡ። 16ዮሐንስ ግን ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ሌላ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እኔ የእርሱን ጫማ ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የበቃሁ አይደለሁም፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። 17እርሱ በአውድማ ላይ እህሉን ከገለባ ለመለየት መንሹን በእጁ ይዞአል፤ ካጣራውም በኋላ ጥሩውን እህል በጐተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” 18እንዲሁም ዮሐንስ በልዩ ልዩ መንገድ ሕዝቡን እየመከረ መልካሙን ዜና ያበሥር ነበር። 19የገሊላውን ገዢ ሄሮድስን ግን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱና ሌላም ብዙ ክፉ ነገር በማድረጉ ገሠጸው። 20ሄሮድስ በክፋት ላይ ክፋት በመጨመር ዮሐንስን ወደ ወህኒ ቤት አስገባው። #ማቴ. 6፥17-18።
የኢየሱስ መጠመቅ
(ማቴ. 3፥13-17ማር. 1፥9-11)
21ሰዎች ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስም ተጠመቀ፤ እርሱ ሲጸልይ ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤ 22መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሆኖ በእርሱ ላይ ወረደ፤ በዚያኑ ጊዜ “አንተ የተወደድክ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። #ዘፍ. 22፥2፤ መዝ. 2፥7፤ ኢሳ. 42፥1፤ ማቴ. 3፥17፤ ማር. 1፥11፤ ሉቃ. 9፥35።
የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሐረግ
(ማቴ. 1፥1-17)
23ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን ሲጀምር፥ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያኽል ሆኖት ነበር፤ ለሕዝቡ ኢየሱስ የዮሴፍ ልጅ ይመስላቸው ነበር፤ ይኸውም ዮሴፍ የዔሊ ልጅ፥ 24ዔሊ የማቲ ልጅ፥ ማቲ የሌዊ ልጅ፥ ሌዊ የሚልኪ ልጅ፥ ሚልኪ የዮና ልጅ፥ ዮና የዮሴፍ ልጅ፥ 25ዮሴፍ የማታትዩ ልጅ፥ ማታትዩ የአሞጽ ልጅ፥ አሞጽ የናሆም ልጅ፥ ናሆም የኤስሊም ልጅ፥ ኤስሊም የናጌ ልጅ፥ 26ናጌ የማአት ልጅ፥ ማአት የማታትዩ ልጅ፥ ማታትዩ የሴሜይ ልጅ፥ ሴሜይ የዮሴፍ ልጅ፥ ዮሴፍ የዮዳ ልጅ፥ 27ዮዳ የዮናን ልጅ፥ ዮናን የሬስ ልጅ፥ ሬስ የዘሩባቤል ልጅ፥ ዘሩባቤል የሰላትያል ልጅ፥ ሰላትያል የኔሪ ልጅ፤ 28ኔሪ የሚልኪ ልጅ፥ ሚልኪ የሐዲ ልጅ፥ ሐዲ የቆሳም ልጅ፥ ቆሳም የኤልሞዳም ልጅ፥ ኤልሞዳም የዔር ልጅ፥ 29ዔር የዮሴዕ ልጅ፥ ዮሴዕ የኤሊዔዛር ልጅ፥ ኤሊዔዛር የዮራም ልጅ፥ ዮራም የማጣት ልጅ፥ ማጣት የሌዊ ልጅ፥ 30ሌዊ የስምዖን ልጅ፥ ስምዖን የይሁዳ ልጅ፥ ይሁዳ የዮሴፍ ልጅ፥ ዮሴፍ የዮናን ልጅ፥ ዮናን የኤልያቂም ልጅ፥ 31ኤልያቄም የሜልያ ልጅ፥ ሜልያ የማይናን ልጅ፥ ማይናን የማጣት ልጅ፥ ማጣት የናታን ልጅ፥ ናታን የዳዊት ልጅ፥ 32ዳዊት የእሴይ ልጅ፥ እሴይ የኢዮቤድ ልጅ፥ ኢዮቤድ የቦዔዝ ልጅ፥ ቦዔዝ የሰልሞን ልጅ፥ ሰልሞን የነአሶን ልጅ፥ 33ነአሶን የዓሚናዳብ ልጅ፥ ዓሚናዳብ የራም ልጅ፥ ራም የአርኒ ልጅ፥ አርኒ የሔጽሮን ልጅ፥ ሔጽሮን የፋሬስ ልጅ፥ ፋሬስ የይሁዳ ልጅ፥ ይሁዳ የያዕቆብ ልጅ፥ 34ያዕቆብ የይስሐቅ ልጅ፥ ይስሐቅ የአብርሃም ልጅ፥ አብርሃም የታራ ልጅ፥ ታራ የናኮር ልጅ፥ 35ናኮር የሰሩግ ልጅ፥ ሰሩግ የረዑ ልጅ፥ ረዑ የፌሌግ ልጅ፥ ፋሌቅ የዔቤር ልጅ፥ ዔቤር የሼላሕ ልጅ፥ 36ሼላሕ የቃይንም ልጅ፥ ቃይንም የአርፋክስድ ልጅ፥ አርፋክስድ የሴም ልጅ፥ ሴም የኖኅ ልጅ፥ ኖኅ የላሜሕ ልጅ፥ 37ላሜሕ የማቱሳላ ልጅ፥ ማቱሳላ የሔኖክ ልጅ፥ ሔኖክ የያሬድ ልጅ፥ ያሬድ የመላልኤል ልጅ፥ መላልኤል የቃይናን ልጅ፥ 38ቃይናን የሄኖስ ልጅ፥ ሄኖስ የሤት ልጅ፥ ሤት የአዳም ልጅ፥ አዳም የእግዚአብሔር ልጅ ነው ይሉ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ