እነሆ፥ ይህ የሆነው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። ፀሐይ ጨለመ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃም ከመካከሉ ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ። ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አባት ሆይ! እነሆ! ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ!” አለ፤ ይህንንም ካለ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች። በዚያ የነበረው መቶ አለቃ፥ የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፥ “በእርግጥ ይህ ሰው ጻድቅ ኖሮአል!” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ነገሩን ለመመልከት እዚያ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ሁሉ የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ በማዘን ደረታቸውን እየመቱ ወደየቤታቸው ተመለሱ። ኢየሱስን በቅርብ ያውቁት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ ይከተሉት የነበሩ ሴቶችም በሩቅ ቆመው ይህን ነገር ይመለከቱ ነበር። የአይሁድ ከተማ በሆነችው በአርማትያስ የሚኖር ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱ ጻድቅና ደግ ሰው ነበረ፤ የአይሁድ ሸንጎ አባልም ነበረ። ይሁን እንጂ በአይሁድ ምክርና ሤራ አልተባበረም፤ እርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት በተስፋ የሚጠባበቅ ሰው ነበረ። ይህ ሰው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ። አስከሬኑንም አውርዶ በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ሰው ባልተቀበረበት ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤ ይህንንም ያደረገው ዓርብ ማታ ለሰንበት ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ነበር። ኢየሱስን ተከትለው ከገሊላ የመጡ ሴቶች ከዮሴፍ ጋር ሄደው መቃብሩን አዩ፤ አስከሬኑም እንዴት እንደ ተቀበረ ተመለከቱ። ወደ ቤታቸውም ተመልሰው ለአስከሬን የሚሆኑ ጥሩ መዓዛ ያለው ቅመምና ሽቶ አዘጋጁ፤ በሕግ መሠረት በሰንበት ቀን ዐርፈው ዋሉ።
የሉቃስ ወንጌል 23 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 23:44-56
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች