ሉቃስ 23:44-56
ሉቃስ 23:44-56 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጊዜው ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፤ የፀሓይ ብርሃን ተከልክሏልና። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ተቀድዶ ለሁለት ተከፈለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፣ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ” አለ፤ ይህንም ብሎ ሞተ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ጻድቅ ነበር” ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ይህንኑ ለማየት በስፍራው ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችም ሁሉ የሆነውን ነገር በተመለከቱ ጊዜ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። ነገር ግን ኢየሱስን በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ እንዲሁም ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉት ሴቶች ይህን እየተመለከቱ ከሩቅ ቆመው ነበር። የአይሁድ ሸንጎ አባል የሆነ፣ አንድ ዮሴፍ የሚባል በጎና ጻድቅ ሰው ነበር። ይህ ሰው በሸንጎው ምክርና ድርጊት አልተባበረም ነበር፤ እርሱም አርማትያስ የምትባል የአይሁድ ከተማ ሰው ሲሆን፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት ይጠባበቅ ነበር። ይህም ሰው ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ በተፈቀደለትም ጊዜ፣ ሥጋውን አውርዶ በበፍታ ገነዘው፤ ከድንጋይ ተፈልፍሎ በተሠራና ገና ማንም ባልተቀበረበት መቃብር ውስጥ አስቀመጠው። ዕለቱ የመዘጋጃ ቀን ነበረ፤ ሰንበትም ሊገባ ነበር። ከገሊላ ጀምሮ ከኢየሱስ ጋር የመጡት ሴቶችም ተከትለው መቃብሩን አዩ፤ ሥጋውንም እንዴት እንዳስቀመጡት ተመለከቱ። ከዚያም ተመልሰው ሽቱና ቅባት አዘጋጁ፤ ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት በሰንበት ቀን ዐረፉ።
ሉቃስ 23:44-56 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፦ አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፦ ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ይህንም ለማየት ተከማችተው የነበሩ ሕዝብ ሁሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። የሚያውቁቱ ግን ሁሉ ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ይህን እያዩ በሩቅ ቆመው ነበር። እነሆም፥ በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ አማካሪም የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ አውርዶም በተልባ እግር ልብስ ከፈነው፥ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው። የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም ሊጀምር ነበረ። ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ።
ሉቃስ 23:44-56 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነሆ፥ ይህ የሆነው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። ፀሐይ ጨለመ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃም ከመካከሉ ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ። ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አባት ሆይ! እነሆ! ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ!” አለ፤ ይህንንም ካለ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች። በዚያ የነበረው መቶ አለቃ፥ የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፥ “በእርግጥ ይህ ሰው ጻድቅ ኖሮአል!” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ነገሩን ለመመልከት እዚያ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ሁሉ የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ በማዘን ደረታቸውን እየመቱ ወደየቤታቸው ተመለሱ። ኢየሱስን በቅርብ ያውቁት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ ይከተሉት የነበሩ ሴቶችም በሩቅ ቆመው ይህን ነገር ይመለከቱ ነበር። የአይሁድ ከተማ በሆነችው በአርማትያስ የሚኖር ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱ ጻድቅና ደግ ሰው ነበረ፤ የአይሁድ ሸንጎ አባልም ነበረ። ይሁን እንጂ በአይሁድ ምክርና ሤራ አልተባበረም፤ እርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት በተስፋ የሚጠባበቅ ሰው ነበረ። ይህ ሰው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ። አስከሬኑንም አውርዶ በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ሰው ባልተቀበረበት ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤ ይህንንም ያደረገው ዓርብ ማታ ለሰንበት ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ነበር። ኢየሱስን ተከትለው ከገሊላ የመጡ ሴቶች ከዮሴፍ ጋር ሄደው መቃብሩን አዩ፤ አስከሬኑም እንዴት እንደ ተቀበረ ተመለከቱ። ወደ ቤታቸውም ተመልሰው ለአስከሬን የሚሆኑ ጥሩ መዓዛ ያለው ቅመምና ሽቶ አዘጋጁ፤ በሕግ መሠረት በሰንበት ቀን ዐርፈው ዋሉ።
ሉቃስ 23:44-56 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፤ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፤ ፀሐይም ጨለመ፤ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ “አባት ሆይ! ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፤” አለ። ይህንንም ብሎ ሞተ። የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ፤” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ይህንም ለማየት ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች በሙሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየመቱ ተመለሱ። እርሱን የሚያውቁት ሁሉ ግን ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ጭምር በሩቅ ቆመው ይህን እያዩ ነበር። እነሆም፥ በጎና ጻድቅ እንዲሁም የሸንጎ አማካሪ የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ በበኩሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። ይኽም ሰው ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን አስከሬን ለመነው፤ አውርዶም በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው። የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም እየጀመረ ነበረ። ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን እንዲሁም አስከሬኑን እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም ዕለት ሕጉ እንዲሚያዘው ዐረፉ።