ፋሲካ የተባለው የቂጣ በዓል የሚከበርበት ቀን ተቃርቦ ነበር፤ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ሕዝቡን ስለ ፈሩ ኢየሱስን ይዘው የሚገድሉበትን ዘዴ በስውር ይፈልጉ ነበር። በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ በሆነው በአስቆሮታዊው ይሁዳ ሰይጣን ገባበት። ስለዚህ ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ቤተ መቅደስ ዘብ አዛዦች ሄዶ ኢየሱስን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ። እነርሱም በነገሩ ተደስተው ገንዘብ ሊሰጡት ተዋዋሉ። በውሉ ተስማምቶ ሕዝቡ ሳያውቅ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ። ኢየሱስ “የፋሲካውን ራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ሲል ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው። እነርሱም “የፋሲካውን ራት የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ከተማ ስትገቡ እነሆ፥ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከትላችሁ ወደሚገባበት ቤት ሂዱ። የቤቱንም ጌታ መምህራችን፥ ‘ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው? ይልሃል’ በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን ተነጥፎ የተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁ።” ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ሄደው፥ ሁሉ ነገር ልክ ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙ፤ የፋሲካውንም ራት በዚያ አዘጋጁ። የእራት ሰዓት በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን የፋሲካ ራት ለመብላት እጅግ እመኝ ነበር፤ የዚህ ነገር እውነተኛ ምሥጢር በእግዚአብሔር መንግሥት ፍጹም ሆኖ እስኪገለጥ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን የፋሲካ ራት ከቶ አልበላም እላችኋለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጽዋውን አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንካችሁ ይህንን ተካፈሉ፤ በእውነት እላችኋለሁ ከአሁን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከዚህ ከወይን ፍሬ የሚገኘውን መጠጥ አልጠጣም።” ቀጥሎም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ፤ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፤ ይህ ለእናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ሰጣቸው። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ ሰጣቸውና እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚፈጸም አዲስ ኪዳን ነው። “ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ፥ ከእኔ ጋር በማእድ ነው። የሰው ልጅ ስለ እርሱ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት!” እነርሱም “ከእኛ መካከል ይህን ነገር የሚያደርግ የትኛው ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ቀጥሎም እነርሱ፥ “ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” እያሉ እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “የዚህ ዓለም ነገሥታት በሕዝቡ ላይ ሥልጣን አላቸው፤ ገዢዎችም የሕዝቡ በጎ አድራጊዎች ይባላሉ፤ እናንተ ግን እንደ እነርሱ ልትሆኑ አይገባም፤ ይልቅስ ከእናንተ መካከል ትልቅ የሆነ እንደ ትንሽ ይሁን፤ አለቃ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን። በማእድ ተቀምጦ ከሚመገበውና ቆሞ ከሚያገለግለው የትኛው ነው ትልቅ? ትልቅ የሚባለው በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ። እናንተ በመከራዬ ጊዜ ሁሉ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ ቈይታችኋል። ስለዚህ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም እናንተን እሾማችኋለሁ። በመንግሥቴም በማእድ ተቀምጣችሁ ትበላላችሁ፤ ትጠጣላችሁ፤ በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱም የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ስምዖን! ስምዖን! እነሆ፥ ገበሬ ስንዴውን ከገለባ አበጥሮ እንደሚለይ እንዲሁም ሰይጣን እናንተን ሊያበጥራችሁ ፈለገ። ነገር ግን የአንተ እምነት እንዳይጠፋ እኔ ለአንተ እጸልያለሁ፤ እንደገና በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና።” ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ለእስራትም ሆነ ለሞት ከአንተ ጋር አብሬ ለመሄድ ዝግጁ ነኝ!” አለ። ኢየሱስ ግን “ጴጥሮስ ሆይ! ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ‘አላውቀውም’ ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “የገንዘብ ቦርሳ፥ ከረጢት፥ ጫማም ሳትይዙ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም የጐደለብን ነገር አልነበረም” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን የገንዘብ ቦርሳም ሆነ ከረጢት ያለው ይያዝ፤ ሰይፍም የሌለው ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። ስለ እኔ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ስለሚገባው ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል በእኔ ላይ መፈጸም አለበት እላችኋለሁ።” ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ እዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ!” አሉት። እርሱም “ይበቃል!” አላቸው።
የሉቃስ ወንጌል 22 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 22:1-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos