የሉቃስ ወንጌል 20:1-26

የሉቃስ ወንጌል 20:1-26 አማ05

አንድ ቀን ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ሕዝቡን ያስተምርና ወንጌልንም ያበሥር በነበረበት ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጡ፤ እነርሱም “በል እስቲ ንገረን እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ወይስ እነዚህን እንድታደርግ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ በሉ እስቲ መልሱልኝ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ነበረን ወይስ ከሰው?” እነርሱም እንዲህ እያሉ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው’ ብንል፥ ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰው ነው’ ብንል ደግሞ ሕዝቡ ሁሉም በዮሐንስ ነቢይነት ስለሚያምኑ በድንጋይ ይወግሩናል።” ስለዚህ “ከየት እንደ ሆነ አናውቅም” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ መናገር ጀመረ፦ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎች አከራየውና ወደ ሌላ አገር ሄደ፤ ሳይመለስም ብዙ ጊዜ ቈየ። ወይኑ ባፈራ ጊዜ የወይኑ ተክል ባለቤት ከፍሬው ድርሻውን እንዲቀበልለት አንድ አገልጋይ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ደብድበው፥ ባዶ እጁን ሰደዱት። እንዲሁም ሌላ አገልጋይ ቢልክ እርሱንም ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት፤ እንደገናም ሦስተኛ አገልጋይ ቢልክ እርሱንም ደብድበው አቈሰሉትና አውጥተው ጣሉት። ከዚህም በኋላ የወይኑ ተክል ባለቤት፦ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልከዋለሁ፤ እርሱን ምናልባት ያከብሩት ይሆናል!’ አለ። ነገር ግን ገበሬዎቹ ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ ‘ይህ ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለው! ርስቱም ለእኛ ይሆናል!’ ስለዚህ ልጁን ከወይኑ ተክል ቦታ ወደ ውጪ አውጥተው ገደሉት። ታዲያ፥ እንግዲህ የወይኑ ተክል ጌታ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? የወይኑ ተክል ባለቤት ራሱ ይመጣል፤ ገበሬዎቹንም ይገድላል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጣል።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ “ይህስ ከቶ አይሁን!” አሉ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ “ታዲያ፥ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማእዘን ራስ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ምንን ያመለክታል? በዚያ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይሰበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበት ሰው ግን ይጨፈለቃል።” የሕግ መምህራንና የካህናት አለቆች ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ ዐውቀው በዚያን ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ስለዚህ ኢየሱስን ለመያዝ ምቹ ጊዜ ይጠብቁ ነበር። ለገዥው ሥልጣንና ፍርድ አሳልፈው ለመስጠት የሚያስችላቸውን የወንጀል ቃል ከእርሱ ለማግኘት ይፈልጉ ነበር፤ ስለዚህ ቅን ሰዎች መስለው፥ በንግግሩ የሚያጠምዱትን ሰላዮች ላኩበት። ሰላዮቹም ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ! አንተ የምትናገረውና የምታስተምረው እውነት መሆኑን እናውቃለን፤ የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት ታስተምራለህ እንጂ ለማንም አታዳላም። እስቲ ንገረን! በሕጋችን መሠረት ለሮም ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እስቲ ገንዘቡን አሳዩኝ፤ በዚህ ገንዘብ ላይ የተቀረጸው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” እነርሱም “የሮም ንጉሠ ነገሥት ነው” አሉት። ኢየሱስም “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በሕዝቡ ፊት በንግግሩ ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ ስለዚህ በመልሱ ተደንቀው ዝም አሉ።