አንድ ቀን ኢየሱስ ሕዝቡን በቤተ መቅደስ ሲያስተምርና ወንጌልን ሲሰብክ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡ። እነርሱም፣ “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን እንደ ሆነ ንገረን፤ ሥልጣንስ የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ እስኪ መልሱልኝ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበር ወይስ ከሰው?” እነርሱም እንዲህ ብለው እርስ በርስ ተመካከሩ፤ “ ‘ከሰማይ’ ብንል፣ ‘ታዲያ፣ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰው’ ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ መሆኑን ስለሚያምኑ በድንጋይ ይወግሩናል።” ስለዚህ፣ “ከየት እንደ ሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎችም አከራየና ወደ ሌላ አገር ሄዶ ብዙ ጊዜ ቈየ። በመከርም ወራት፣ ከወይኑ ፍሬ እንዲልኩለት ባሪያውን ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ባሪያውን ደብድበው ባዶ እጁን ሰደዱት። ቀጥሎም ሌላ ባሪያውን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት። አሁንም ቀጥሎ ሦስተኛ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ አቍስለው ወደ ውጭ ጣሉት። “የወይኑ ተክል ባለቤትም፣ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? እስኪ ደግሞ የምወድደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን ያከብሩት ይሆናል’ አለ። “ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህ እኮ ወራሹ ነው፣ ኑና እንግደለው፤ በዚህም ርስቱ የእኛ ይሆናል’ እየተባባሉ ተመካከሩ፤ ከወይኑም ተክል ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “እንግዲህ የወይኑ ተክል ባለቤት ምን ያደርጋቸዋል? መጥቶ እነዚያን ገበሬዎች ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም ተክል ቦታ ለሌሎች ይሰጣል።” ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “እንዲህ ያለውንስ አያምጣው” አሉ። ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ታዲያ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ትርጕሙ ምንድን ነው? በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩም በላዩ የሚወድቅበት ሁሉ ይደቅቃል።” ጸሐፍትና የካህናት አለቆችም ይህን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ መሆኑን ስላወቁ፣ በዚያ ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ኢየሱስን አሳልፈው ለገዢው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት። ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን። ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እስኪ አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ በላዩ ያለው የማን መልክና ጽሕፈት ነው?” እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” ብለው መለሱለት። እርሱም፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ስለዚህ በተናገረው ቃል በሕዝቡ ፊት ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም ተገርመው ዝም አሉ።
ሉቃስ 20 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 20
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 20:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች