በዚያን ጊዜ በሮማውያን ግዛት ያሉ ሰዎች ሁሉ እንዲቈጠሩ ከሮማው ንጉሠ ነገሥት አውግስጦስ ታወጀ። ይህም የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ በተደረገ ጊዜ ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ ነበር። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ስሙን ለማስመዝገብ ወደ ትውልድ አገሩ ይሄድ ነበር። ዮሴፍም በትውልዱ የዳዊት ዘር ስለ ነበረ በገሊላ ምድር ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ በይሁዳ ምድር ወደምትገኘው ወደ ዳዊት ከተማ፥ ወደ ቤተልሔም ሄደ፤ ሊመዘገብ የሄደውም ፀንሳ ከነበረችው ከእጮኛው ከማርያም ጋር ነበር። በቤተልሔም ከተማ ሳሉ ማርያም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ። በዚያም የበኲር ልጅዋን ወለደች፤ በመታቀፊያ ጨርቅ ጠቀለለችው፤ በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ስላላገኙ በበረት በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ አስተኛችው። በዚያም አካባቢ፥ በሜዳ ላይ ሌሊት መንጋቸውን እየጠበቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። እነሆ፥ ለእነርሱ የጌታ መልአክ ታያቸው፤ የጌታም የክብር ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ እነርሱም በጣም ፈሩ፤ መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ! ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን መልካም ዜና ይዤላችሁ መጥቻለሁ፤ እነሆ! ዛሬ በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። ምልክቱም ይህ ነው፤ በመታቀፊያ ጨርቅ የተጠቀለለ ሕፃን በበረት ውስጥ በግርግም ላይ ተኝቶ ታገኛላችሁ።” በድንገት ብዙ የሰማይ መላእክት ከመልአኩ ጋር አብረው ታዩ፤ እግዚአብሔርንም በማመስገን፥ “በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን! በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን!” ይሉ ነበር። መላእክቱ ተለይተዋቸው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ ወደ ቤተልሔም እንሂድ፤ አሁን የተፈጸመውንና ጌታ የገለጠልንን ነገር እንይ” ተባባሉ። በፍጥነት ሄደው ማርያምንና ዮሴፍን አገኙ፤ ሕፃኑንም በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ ተኝቶ አዩት። ሕፃኑንም ካዩ በኋላ መልአኩ ስለ እርሱ የነገራቸውን አወሩ። ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ ባወሩላቸው ነገር ተደነቁ። ማርያም ግን፥ ይህን ሁሉ ነገር በልብዋ ይዛ ታሰላስለው ነበር። እረኞቹ፥ ሁሉ ነገር መልአኩ እንዳላቸው ሆኖ በማየታቸውና በመስማታቸው፥ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ፥ ወደ ስፍራቸው ተመለሱ። ከስምንት ቀን በኋላ ሕፃኑ በሚገረዝበት ሥነ ሥርዓት ላይ፥ ስሙ “ኢየሱስ” ተብሎ ተጠራ። ይህም ገና ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ያወጣለት ስም ነው። በሕግ መሠረት፥ የመንጻት ሥርዓት የሚፈጸምበት ጊዜ ደረሰ፤ ስለዚህ ማርያምና ዮሴፍ ሕፃኑን በጌታ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ሄዱ። ይህንንም ያደረጉት በጌታ ሕግ “ወንድ የሆነ በኲር ልጅ ሁሉ ለጌታ ተሰጥቶ የተቀደሰ ይሆናል” የሚል ትእዛዝ ተጽፎ ስለ ነበር ነው። እንዲሁም በጌታ ሕግ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ለመሥዋዕት ማቅረብ ይገባል” የሚል ትእዛዝ ነበረ።
የሉቃስ ወንጌል 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 2:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች