የሉቃስ ወንጌል 15:17-24

የሉቃስ ወንጌል 15:17-24 አማ05

በዚህ ጊዜ ልጁ ስሕተቱን ተገንዝቦ እንዲህ ሲል አሰበ፤ ‘በአባቴ ቤት ተቀጥረው የሚሠሩ አገልጋዮች እንጀራ እስኪጠግቡ በልተው የሚተርፋቸው ስንት ናቸው! እኔ ግን እዚህ በረሀብ መሞቴ ነው፤ ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፦ አባባ፥ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ያንተ ልጅ ልባል አይገባኝም፤ ነገር ግን ከቅጥረኞች አገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ ልበለው።’ ስለዚህ ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ። “አባቱም ገና በሩቅ ሳለ ልጁን አየው፤ ራርቶለትም ወደ እርሱ ሮጠ፤ ዕቅፍ አድርጎም ሳመው። ልጁም ‘አባባ፥ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም’ አለ። አባቱ ግን አገልጋዮቹን ጠርቶ እንዲህ አለ፦ ‘ቶሎ ብላችሁ ከሁሉ የበለጠውን ልብስ አምጡና አልብሱት! በጣቱ ቀለበት፥ በእግሩም ጫማ አድርጉለት! የሰባውን ወይፈን አምጡና ዕረዱ! እንብላ! እንደሰት! ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፥ እነሆ፥ አሁን በሕይወት አለ፤ ጠፍቶ ነበር፤ ተገኘ’፤ መደሰትም ጀመሩ።