የሉቃስ ወንጌል 15
15
ጠፍቶ የተገኘው በግ ምሳሌ
(ማቴ. 18፥12-14)
1ቀራጮችና ኃጢአተኞች ሁሉ ትምህርቱን ለመስማት ተሰብስበው ወደ ኢየሱስ መጥተው ነበር። 2ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ግን ይህን አይተው፦ “ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር አብሮ ይበላል” እያሉ በኢየሱስ ላይ አጒረመረሙ። #ሉቃ. 5፥29-30። 3ስለዚህም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው።
4“ከእናንተ መካከል መቶ በግ ያለው ሰው ከመቶዎቹ አንድ በግ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በዱር ትቶ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ለመፈለግ የማይሄድ ማነው? 5ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በትከሻው ይሸከመውና መልሶ ያመጣዋል። 6ወደ ቤቱም በደረሰ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ ‘የጠፋውን በጌን አግኝቼአለሁና ደስ ብሎኛል ደስ ይበላችሁ!’ ይላቸዋል። 7ንስሓ መግባት ከማያስፈልጋቸው ዘጠና ዘጠኝ ደጋግ ሰዎች ይልቅ ንስሓ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ ምክንያት በሰማይ እንዲሁ ደስታ ይሆናል እላችኋለሁ።”
ጠፍቶ የተገኘው የብር መሐለቅ
8ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ዐሥር የብር መሐለቅ ያላት ሴት ከዐሥሩ አንዱ መሐለቅ ቢጠፋባት መብራት አብርታ፥ ቤትዋን ጠርጋ የጠፋባትን መሐለቅ እስክታገኝ ድረስ በጥንቃቄ አትፈልገውምን? 9ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ ‘የጠፋውን መሐለቄን አግኝቼዋለሁና ደስ ብሎኛል ደስ ይበላችሁ!’ ትላቸዋለች። 10ንስሓ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ ምክንያት በሰማይ በእግዚአብሔር መላእክት ዘንድ እንዲሁ ደስታ ይሆናል እላችኋለሁ።”
ጠፍቶ የተገኘው ልጅ
11ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ 12ታናሽዮው አባቱን ‘አባባ፥ ከሀብትህ ከፍለህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው። ስለዚህ አባትየው ሀብቱን ለሁለት ልጆቹ አካፈለ። 13ከጥቂት ቀን በኋላ ታናሽዮው ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም አገር ገንዘቡን ሁሉ በከንቱ አባከነ። 14ገንዘቡንም ሁሉ ከጨረሰ በኋላ በዚያ አገር ብርቱ ራብ በመግባቱ በችግር ላይ ወደቀ። 15ስለዚህ ከዚያ አገር ሰዎች ወደ አንዱ ተጠጋ፤ ሰውየውም የዐሣማ እረኛ አደረገው። 16ዐሣማዎቹ ከሚመገቡት ብጣሪ ዐሠር ሆዱን ለመሙላት ይመኝ ነበር፤ ግን ይህንኑ እንኳ የሚሰጠው አልነበረም። 17በዚህ ጊዜ ልጁ ስሕተቱን ተገንዝቦ እንዲህ ሲል አሰበ፤ ‘በአባቴ ቤት ተቀጥረው የሚሠሩ አገልጋዮች እንጀራ እስኪጠግቡ በልተው የሚተርፋቸው ስንት ናቸው! እኔ ግን እዚህ በረሀብ መሞቴ ነው፤ 18ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፦ አባባ፥ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ 19ከእንግዲህ ወዲህ ያንተ ልጅ ልባል አይገባኝም፤ ነገር ግን ከቅጥረኞች አገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ ልበለው።’ 20ስለዚህ ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ።
“አባቱም ገና በሩቅ ሳለ ልጁን አየው፤ ራርቶለትም ወደ እርሱ ሮጠ፤ ዕቅፍ አድርጎም ሳመው። 21ልጁም ‘አባባ፥ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም’ አለ። 22አባቱ ግን አገልጋዮቹን ጠርቶ እንዲህ አለ፦ ‘ቶሎ ብላችሁ ከሁሉ የበለጠውን ልብስ አምጡና አልብሱት! በጣቱ ቀለበት፥ በእግሩም ጫማ አድርጉለት! 23የሰባውን ወይፈን አምጡና ዕረዱ! እንብላ! እንደሰት! 24ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፥ እነሆ፥ አሁን በሕይወት አለ፤ ጠፍቶ ነበር፤ ተገኘ’፤ መደሰትም ጀመሩ።
25“በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ ለሥራ ወደ እርሻ ወጥቶ ነበር፤ ተመልሶ ሲመጣ ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ፤ 26ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ ‘ምንድን ነው ነገሩ?’ ብሎ ጠየቀው። 27አገልጋዩም ‘ወንድምህ ተመልሶ ስለ መጣ ነው፤ አባትህ በደኅና ስላገኘው የሰባውን ወይፈን ዐርዶለታል’ አለው።
28“ታላቅ ወንድሙም በጣም ተቈጥቶ፥ ‘ወደ ቤት አልገባም’ አለ። ስለዚህ አባቱ ወደ ደጅ ወጥቶ እንዲገባ ለመነው፤ 29ልጁ ግን ለአባቱ እንዲህ ሲል መለሰ፤ ‘እነሆ! ይህን ያኽል ዓመት አገለገልኩህ፤ ከትእዛዝህም ከቶ ዝንፍ ብዬ አላውቅም፤ ታዲያ እኔ ከጓደኞቼ ጋር የምደሰትበት አንድ ጠቦት እንኳ ሰጥተኸኝ አታውቅም! 30ይህ ልጅህ ግን ሀብትህን ከአመንዝራ ሴቶች ጋር አባክኖ በተመለሰ ጊዜ የሰባውን ወይፈን ዐረድክለት።’ 31አባቱም እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነ ሁሉ የአንተ ነው። 32ይህ ወንድምህ ግን ሞቶ ነበር፤ አሁን በሕይወት አለ፤ ጠፍቶ ነበር፤ አሁን ተገኘ፤ ስለዚህ በጣም ልንደሰት ይገባናል።’ ”
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 15: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997