የሉቃስ ወንጌል 15:1-10

የሉቃስ ወንጌል 15:1-10 አማ05

ቀራጮችና ኃጢአተኞች ሁሉ ትምህርቱን ለመስማት ተሰብስበው ወደ ኢየሱስ መጥተው ነበር። ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ግን ይህን አይተው፦ “ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር አብሮ ይበላል” እያሉ በኢየሱስ ላይ አጒረመረሙ። ስለዚህም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው። “ከእናንተ መካከል መቶ በግ ያለው ሰው ከመቶዎቹ አንድ በግ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በዱር ትቶ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ለመፈለግ የማይሄድ ማነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በትከሻው ይሸከመውና መልሶ ያመጣዋል። ወደ ቤቱም በደረሰ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ ‘የጠፋውን በጌን አግኝቼአለሁና ደስ ብሎኛል ደስ ይበላችሁ!’ ይላቸዋል። ንስሓ መግባት ከማያስፈልጋቸው ዘጠና ዘጠኝ ደጋግ ሰዎች ይልቅ ንስሓ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ ምክንያት በሰማይ እንዲሁ ደስታ ይሆናል እላችኋለሁ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ዐሥር የብር መሐለቅ ያላት ሴት ከዐሥሩ አንዱ መሐለቅ ቢጠፋባት መብራት አብርታ፥ ቤትዋን ጠርጋ የጠፋባትን መሐለቅ እስክታገኝ ድረስ በጥንቃቄ አትፈልገውምን? ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ ‘የጠፋውን መሐለቄን አግኝቼዋለሁና ደስ ብሎኛል ደስ ይበላችሁ!’ ትላቸዋለች። ንስሓ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ ምክንያት በሰማይ በእግዚአብሔር መላእክት ዘንድ እንዲሁ ደስታ ይሆናል እላችኋለሁ።”