የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 14:15-24

የሉቃስ ወንጌል 14:15-24 አማ05

በማእድ ተቀምጠው ከነበሩት አንዱ ኢየሱስ የተናገረውን ሰምቶ “በእግዚአብሔር መንግሥት በማእድ መቀመጥ የሚችል እንዴት የታደለ ነው!” አለ። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለው፤ “አንድ ሰው ትልቅ የእራት ግብዣ አዘጋጅቶ፥ ብዙ ሰዎችን ጠራ፤ የግብዣው ሰዓት በደረሰ ጊዜ፥ ‘እነሆ፥ ሁሉ ነገር ተዘጋጅቶአልና ወደ ግብዣው ኑ!’ ብሎ እንዲነግራቸው ጋባዡ አገልጋዩን ወደ ተጠሩት ሰዎች ላከው። ነገር ግን እያንዳንዱ ተጋባዥ ከግብዣው ለመቅረት ምክንያት መስጠት ጀመረ፤ አንዱ ‘መሬት ስለ ገዛሁ ሄጄ ማየት አለብኝ፤ ስለዚህ መምጣት አልችልምና ይቅርታ አድርግልኝ’ አለው። ሌላው ‘አምስት ጥንድ በሬዎች ስለ ገዛሁ እነርሱን መፈተን አለብኝ፤ ስለዚህ መምጣት አልችልምና ይቅርታ አድርግልኝ’ አለ። ሌላው ደግሞ ‘ሚስት አግብቼ ሙሽራ ስለ ሆንኩ ልመጣ አልችልም’ አለ። “አገልጋዩም ወደ ቤት ተመልሶ ይህን ሁሉ ለጌታው ነገረው፤ የቤቱም ጌታ ተቈጥቶ አገልጋዩን ‘ቶሎ ብለህ ወደ ከተማው ጐዳናዎችና ስላች መንገዶች ሂድ፤ ድኾችን፥ አካለ ስንኩሎችን፥ ዕውሮችን፥ አንካሶችንም ጠርተህ አምጣልኝ’ አለው። አገልጋዩም ተመልሶ መጣና ጌታውን ‘ጌታዬ ሆይ! እነሆ፥ ያዘዝከኝን ሁሉ ፈጽሜአለሁ፤ ሆኖም ገና ትርፍ ቦታ አለ’ አለው። ስለዚህ የቤቱ ጌታ አገልጋዩን እንዲህ አለው፦ ‘ቤቴ እንዲሞላ ወደ ገጠር በሚወስዱት ጐዳናዎችና ስላች መንገዶች ሂደህ ሌሎች እንዲመጡ አድርግ! ከእነዚያ ተጠርተው ከነበሩት ሰዎች አንዱ እንኳ ድግሴን አይቀምስም!’ አለ እላችኋለሁ።”