የሉቃስ ወንጌል 14:1-24

የሉቃስ ወንጌል 14:1-24 አማ05

በሰንበት ቀን፥ ኢየሱስ ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት ምሳ ሊበላ ገባ፤ ፈሪሳውያን እርሱ የሚያደርገውን ለማየት ይጠባበቁት ነበር። በዚያን ጊዜ በሕመም ምክንያት መላ ሰውነቱ ያበጠበት አንድ ሰው በኢየሱስ ፊት ነበር። ኢየሱስም የሕግ መምህራንንና ፈሪሳውያንን “በሰንበት ቀን መፈወስ በሕግ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱ ግን ምንም ሳይመልሱ ዝም አሉ፤ ኢየሱስ የታመመውን ሰው ይዞ ፈወሰውና አሰናበተው። ቀጥሎም ኢየሱስ፦ “ከእናንተ በሰንበት ቀን ልጁ ወይም በሬው በጒድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት ወዲያውኑ የማያወጣው ማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱ ግን ምንም መልስ መስጠት አልቻሉም። ኢየሱስ ለግብዣ የተጠሩ ሰዎች የክብር ስፍራ ለመያዝ ሲሽቀዳደሙ አየ፤ ስለዚህ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ሰው ለሠርግ ግብዣ ሲጠራህ በክብር ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ የበለጠ ክብር ያለው ሰው ተጠርቶ ይሆናል፤ ታዲያ፥ ሁለታችሁንም የጋበዛችሁ ሰው ወደ አንተ መጥቶ፦ ‘ይህን ስፍራ ለዚህ ሰው ልቀቅለት’ ይልሃል፤ ያን ጊዜ በታላቅ ኀፍረት ወደ ዝቅተኛው ቦታ ወርደህ ትቀመጣለህ። ነገር ግን ለግብዣ ስትጠራ ሄደህ በዝቅተኛ ስፍራ ተቀመጥ፤ በዚያን ጊዜ የጠራህ ሰው ወደ አንተ መጥቶ፦ ‘ወዳጄ ሆይ! ወደ ከፍተኛው ስፍራ ወጥተህ ተቀመጥ’ ይልሃል፤ ያን ጊዜም በሌሎች ተጋባዦች ሁሉ ፊት ክብር ታገኛለህ። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል፤ ራሱን የሚያዋርድ ግን ከፍ ይላል።” ኢየሱስ ጋባዡን ሰው ደግሞ እንዲህ አለው፦ “የምሳ ወይም የእራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ብድራቸውን ለመመለስ በተራቸው የሚጋብዙህን ወዳጆችህን፥ ወንድሞችህን፥ ዘመዶችህን፥ ሀብታሞች ጐረቤቶችህንም አትጥራ፤ ነገር ግን ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድኾችን፥ አካለ ስንኩሎችን፥ ሽባዎችን፥ ዕውሮችንም ሰዎች ጥራ። ይህን ብታደርግ እነርሱ ውለታ ለመክፈል ስለማይችሉ የተባረክህ ትሆናለህ። በጻድቃን ትንሣኤ ጊዜም እግዚአብሔር ይከፍልሃል።” በማእድ ተቀምጠው ከነበሩት አንዱ ኢየሱስ የተናገረውን ሰምቶ “በእግዚአብሔር መንግሥት በማእድ መቀመጥ የሚችል እንዴት የታደለ ነው!” አለ። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለው፤ “አንድ ሰው ትልቅ የእራት ግብዣ አዘጋጅቶ፥ ብዙ ሰዎችን ጠራ፤ የግብዣው ሰዓት በደረሰ ጊዜ፥ ‘እነሆ፥ ሁሉ ነገር ተዘጋጅቶአልና ወደ ግብዣው ኑ!’ ብሎ እንዲነግራቸው ጋባዡ አገልጋዩን ወደ ተጠሩት ሰዎች ላከው። ነገር ግን እያንዳንዱ ተጋባዥ ከግብዣው ለመቅረት ምክንያት መስጠት ጀመረ፤ አንዱ ‘መሬት ስለ ገዛሁ ሄጄ ማየት አለብኝ፤ ስለዚህ መምጣት አልችልምና ይቅርታ አድርግልኝ’ አለው። ሌላው ‘አምስት ጥንድ በሬዎች ስለ ገዛሁ እነርሱን መፈተን አለብኝ፤ ስለዚህ መምጣት አልችልምና ይቅርታ አድርግልኝ’ አለ። ሌላው ደግሞ ‘ሚስት አግብቼ ሙሽራ ስለ ሆንኩ ልመጣ አልችልም’ አለ። “አገልጋዩም ወደ ቤት ተመልሶ ይህን ሁሉ ለጌታው ነገረው፤ የቤቱም ጌታ ተቈጥቶ አገልጋዩን ‘ቶሎ ብለህ ወደ ከተማው ጐዳናዎችና ስላች መንገዶች ሂድ፤ ድኾችን፥ አካለ ስንኩሎችን፥ ዕውሮችን፥ አንካሶችንም ጠርተህ አምጣልኝ’ አለው። አገልጋዩም ተመልሶ መጣና ጌታውን ‘ጌታዬ ሆይ! እነሆ፥ ያዘዝከኝን ሁሉ ፈጽሜአለሁ፤ ሆኖም ገና ትርፍ ቦታ አለ’ አለው። ስለዚህ የቤቱ ጌታ አገልጋዩን እንዲህ አለው፦ ‘ቤቴ እንዲሞላ ወደ ገጠር በሚወስዱት ጐዳናዎችና ስላች መንገዶች ሂደህ ሌሎች እንዲመጡ አድርግ! ከእነዚያ ተጠርተው ከነበሩት ሰዎች አንዱ እንኳ ድግሴን አይቀምስም!’ አለ እላችኋለሁ።”